በማያ ከተማ አስተዳደር በምናከናውነው የሌማት ትሩፋት ተግባራት ተጠቃሚነታችንን እያረጋገጥን ነው - የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
በማያ ከተማ አስተዳደር በምናከናውነው የሌማት ትሩፋት ተግባራት ተጠቃሚነታችንን እያረጋገጥን ነው - የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች
ማያ፤ ታህሳስ 1/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ማያ ከተማ አስተዳደር በተሰማሩበት የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከራሳቸው አልፈው የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆናቸውን በከተማው የልማቱ ተሳታፊዎች ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በይፋ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የቤተሰብ የምግብ ሥርዓት ከማሻሻል አልፎ ለበርካቶች የሥራ እድል ፈጥሯል፣ በገበያም የምርቶችን አቅርቦት በማብዛት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ነው።
በኦሮሚያ ክልል ማያ ከተማ አስተዳደርም በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በመከናወን ላይ ያሉ ተግባራት በርካቶችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ናቸው።
በከተማው በመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቆ በከብት ማድለብና እርባታ ከስድስት ጓደኞቹ ጋር እየሰራ የሚገኘው የከተማው ወጣት ደቻሳ አህመድ ነው።
ወጣት ደቻሳ እንደሚገልጸው፤ የከተማ አስተዳደሩ ባመቻቸላቸው የስራ ቦታ በመጠቀም በቀን 80 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ እስከ ሶስት ሺህ ብር የተጣራ ትርፍ ያገኛሉ።
ከዚህ ቀደም የነበሯቸውን 18 በሬዎች መሸጣቸውንና በምትኩም የእርባታ ላሞችን በመግዛት ስራ መጀመራቸውን የተናገረው ደግሞ ሌላው ወጣት ቦና ሸሪፍ ነው።
እነዚህ የውጭ ዝርያ ያላቸው አምስት ላሞችን እንደሚንከባከብና እያንዳንዳቸው ጠዋት ላይ 15 ሊትር ከሰዓት ከ13 እስከ 14 አልፎም እስከ 20 ሊትር ወተት በመስጠት ተጠቃሚ እያደረጉን ይገኛሉ ሲል ተናግሯል።
ከከብት ማድለብና ከወተት ላሞች የተሻለ ጥቅም እንደሚያገኙና ወደፊትም ስራውን አጠናክረው በመስራት የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ተስፋ እንዳላቸው የሚናገሩት ደግሞ አቶ ሙስጠፋ ሀሩን ናቸው።
የማያ ከተማ ከንቲባ ኢፍራህ ወዚር(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከተማዋን የበለጸገች ለማድረግና የነዋሪዎችንና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የሌማት ትሩፋት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌማት ትሩፋት ስራውም ባለሃብቶች፣ በከተማና ገጠር በማህበር የተደራጁ ወጣቶችና አርሶ አደሮች እንዲሁም ግለሰቦችን ጨምሮ ከ300 በላይ ክላስተሮች በሌማት ትሩፋት ስራው እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የሚከናወኑ የሌማት ትሩፋት ስራዎች እናቶችና ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ በቀላሉ እንዲያገኙ ከማስቻል ባለፈ ከ11ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ተገኝተው የመርሃ ግብሩን ተግባራት የተመለከለቱት የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ ኤሊያስ ኡመታ እንዳሉት፤ መንግስት ምርትና ምርታማነትን ለማጎልበት የተለያዩ ኢንሼቲቮችን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ ነው።
በከተሞች አካባበቢ በሌማት ትሩፋትና በከተማ ግብርና የሚከናወኑ ስራዎች ህብረተሰቡን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እያሸጋገሩ መሆኑን መመልከታቸውን በማንሳት።
በተለይም በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞን እንዲሁም በማያ ከተማ አስተዳደር በጠባብ መሬት በጓሮ አትክልት፣ በዶሮና ከብት እርባታ፣ በማር ምርትና በከብት ማድለብ እንዲሁም በሌሎች ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን መመልከታቸውን አውስተዋል።
የሌማት ትሩፋቱ ስራ በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተመረቁ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻሉንና የከተማው ነዋሪ ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ማስቻሉን ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ነዋሪውን ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት ስራን በቀጣይም ማስፋት እንደሚገባ አመልክተዋል።