የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በተቋረጡ ፕሮጀክቶች የደረሰውን የኃብት ብክነት በፍጥነት እንዲያርም ምክር ቤቱ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በተቋረጡ ፕሮጀክቶች የደረሰውን የኃብት ብክነት በፍጥነት እንዲያርም ምክር ቤቱ አሳሰበ
አዲስ አበባ፤ 30/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በተቋረጡ ፕሮጀክቶች የደረሰውን የኃብት ብክነት ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መንገድ እርምጃ እንዲወስድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የሥራ ተቋራጭ ብቃትና ምዘና፣ ክትትል እና የሰራተኞች የሙያ ደህንነትና ጤንነት አጠባበቅ አፈፃጸምን በተመለከተ በቀረበው የክዋኔ ሪፖርት መክሯል።
በፌዴራል በጀት የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን የያዙ ሥራ ተቋራጮች ፕሮጀክቶቹን ሳያጠናቅቁ አሊያም አፈፃጸማቸው ሳይታይ በሌላ ጨረታ ላይ እንዳይወዳደሩ የሚከለክል የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቶ ቁጥጥርና ክትትል ባለማድረጉ ከአንድ በላይ ፕሮጀክቶችን ይዘው ያቋረጡ መኖራቸውን በኦዲት ሪፖርቱ ተገልጿል።
በዚህም የውል ዋጋቸው ከ10 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ የሆኑ 12 ፕሮጀክቶች በሁለት ሥራ ተቋራጮች የተያያዙ እንደሆኑ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
በአገሪቱ የተቋረጡ ፕሮጀክትን አጠቃላይ መረጃ በመያዝ ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት አለመሰራቱንም እንዲሁ።
በናሙና ከታዩ 41 ፕሮጀክቶች ውስጥ 13 ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ የገቡ ቢሆንም 28ቱ ኦዲቱ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ወደ ግንባታ አለመግባታቸውን ሪፖርቱ ያሳያል።
የፕሮጀክቶች መቋረጥ በመንግስት ኃብት ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት ማስከተሉ በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል።
በናሙና ከታዩ 41 የተቋረጡ ፕሮጀክቶች ተመልሰው ወደ ግንባታ የገቡትን 13 ፕሮጀክቶች መሰረት በማድረግ ፕሮጀክቶቹ በመጀመሪያ ውላቸው ባለመጠናቀቃቸው ከ16 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በመንግሥት ላይ ተጨማሪ ወጪ ማስከተላቸውን የኦዲት ሪፖርቱ አረጋግጧል።
ከተቋረጡ ፕሮጀክቶች ለ25ቱ ከተከፈለ ቅድመ ክፍያ ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ተመላሽ አለመደረጉንም ሪፖርቱ ያሳያል።
ቋሚ ኮሚቴው በእነዚህና ሌሎች በኦዲት ግኝቶች ላይ በዝርዝር የቀረቡ የኦዲት ግኝት ላይ የተወሰደውን የእርምት እርምጃ ማብራሪያ ጠይቋል።
የተቋሙ ኃላፊዎች በኦዲት ግኝቱ መሰረት የተወሰዱ የእርምት እርምጃዎችና በሂደት ላይ ያሉትን በምላሻቸው ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳሬክተር ሙአዝ በድሩ(ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ አንድ ሥራ ተቋራጭ የሚይዘው ፕሮጀክት ብዛት የሚከለክል አሰራር አለመኖሩን ለችግሩ መፈጠር ምክንያት አድረገው አቅርበዋል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው ፕሮጀክቶች በመቋረጣቸውና ወደ ሌላ በመተላለፋቸው መንግሥትን ከ16 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ እንዲዳረግ ያደረገው የፕሮጀክት ማንጅመንት ማነስ ነው ብለዋል።
የፌደራል ምክትል ዋና ኦዲተር አበራ ታደሰ ባለሥልጣኑ በወሰዳቸው የማስተካከያ እርምት እርምጃ ላይ በቁጥጥር ኦዲት እንደሚረጋገጥ ገልጸዋል።
የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አራሬ ሞሲሳ በኦዲት ግኝቱ መሰረት በፕሮጀክት መቋረጥ ምክንያት በኃብት ላይ የደረሰውን ብክነት እንዲያስተካክል ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ባለስልጣኑ ተመላሽ የሚደረጉና ሌሎች ማስተካከያዎችን በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎችን እቅድ አውጥቶ እስከ ታህሳስ 15 እንዲያቀርብ አሳስበዋል።