የኢትዮጵያ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ አስተማማኝ፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ አሰራርን የሚከተል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ አስተማማኝ፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ አሰራርን የሚከተል ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ በሁሉም መለኪያ አስተማማኝ፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ አሰራርን የሚከተል መሆኑን የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ጄኔራል ሉሲ ምቡጓ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የተመሰረተበትና የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ማቋቋሚያ ስምምነት የተፈረመበት 80ኛ ዓመት በዓል በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።
በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ጄኔራል ሉሲ ምቡጓ፤ ዓለም አቀፉን የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ከመሰረቱ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በየጊዜው እድገትና መሻሻል በማሳየት በሁሉም መለኪያ አስተማማኝና ቀልጣፋ አሰራርን የሚከተል መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአስተማማኝ የበረራ አገልግሎት በተለይም አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር በማገናኘት የላቀ ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከ112 ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ የአየር አገልግሎት ስምምነቶችን(BASA) መፈራረሙን አንስተዋል።
በአቪዬሽን ዘርፍ ኢትዮጵያ ደህንነቱ የተጠበቀ ቀልጣፋ ዘመናዊ አገልግሎት እየሰጠች መሆኑን አስታውሰው ከሌሎች አባል ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ ጌታቸው መንግስቴ፤ ለኢትዮጵያ ባህል፣ ቱሪዝም፣ ንግድና ኢንዱስትሪ እድገት የአቪዬሽን ዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
የአቪዬሽን ዘርፍ ቀጣይ የአለም ህዝቦች ትስስር ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልፀው፤ ኢትዮጵያም ከዚሁ አንፃር ሚናዋን በላቀ መልኩ እየተወጣች መሆኑን አስረድተዋል።