በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለልማት ተነሺዎች ከ8 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለልማት ተነሺዎች ከ8 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለልማት ተነሺዎች ከ8 ሺህ በላይ ቤቶች መገንባታቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
ለካዛንችስ ልማት ተነሺዎች የተዘጋጀው የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር ዛሬ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በመዲናዋ በሁሉም አካባቢዎች ለልማት ተነሺዎች ከ8 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተዋል።
ለግንባታውም ከ10 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።
ለልማት ተነሺዎች ደግሞ ከ12 ቢሊየን ብር በላይ ካሳ መከፈሉንና ከ100 ሄክታር በላይ መሬት ደግሞ ለምትክ ቦታ መተላለፉን ጠቁመዋል።
አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እና አበባ ለማድረግ መሰረተ ልማት ከማሟላት በተጨማሪ የሰው አኗኗርን ማሻሻል እና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በምቹ የመኖሪያ አካባቢዎች ቤቶችን በመገንባት የተሳለ ህይወት እንዲመሩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ለአብነትም ከካዛንቺስ አካባቢ በመነሳት በገላን ጉራ በምቹ ሁኔታ እንዲኖሩ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በገላን ጉራ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የተቀናጀ የልማት መንደሩ 6 ሺህ 500 ነዋሪዎችን የያዘ መኖሪያ መንደር መሆኑን ጠቅሰው አካባቢው 1 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአስፋልት መንገድ ያካተተ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከ20 በላይ አውቶቡሶችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል ተርሚናል፣ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ የተገነቡ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶች ከእነምገባ ማዕከሉ መያዙን ነው ከንቲባዋ የገለጹት።
በሶስት ፈረቃ ለ270 እናቶች የስራ እድል የፈጠረ የእንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካ እና 500 አረጋውያንና አቅመ ደካሞችን በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የሚያስችል የምገባ ማዕከል በልማት መንደሩ እንደተገነባም አመልክተዋል።
የልማት መንደሩ በቀን 60ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም ያለው የዳቦ ፋብሪካ እና የእህል ወፍጮዎችን የያዘ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሁሉም ልማቶች ላይ ሰውን መሰረት ያደረገና የሰውን ኑሮ መቀየር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገ ትውልድ ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አለማየሁ ሚጃና፤ ገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር የተሰራው ስራ ለመዲናዋ ሰው ተኮር ስራዎች ጥሩ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የካዛንችስ አካባቢ የልማት ተነሺዎች በበኩላቸው በገላን ጉራ የተሰራላቸው መሰረተ ልማት በኑሯቸው ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።
በፊት ከነበሩበት የማይመች አኗኗር በመውጣት ወደ ምቹ ቦታ በመምጣታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።