ቀጥታ፡

በኢትዮጵያና በቼክ ሪፐብሊክ መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና በቼክ ሪፐብሊክ መካከል በኢኮኖሚ፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በውኃና ኢነርጂ ፣ በማምረቻ ዘርፍ እንዲሁም በመከላከያ ኢንዱስትሪ ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከቼክ ሪፐብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪያን ጁሬስካ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይም ዶክተር ጌዴዮን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በውኃና ኢነርጂ፣ በማምረቻ እንዲሁም በመከላከያ ኢንዱስትሪ ትብብር ለማጠናከር መሥራት እንደሚገባ አንስተዋል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዘመናትን ያስቆጠረና ትርጉም ባለው አጋርነት የተጋመደ መሆኑን በማንሳት በኢትዮጵያ በርካታ ኢንዱስትሪዎች በቼክ ሪፐብሊክ የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ መገንባታቸውንም እንደ ማሳያ ገልጸዋል።


 

ዶክተር ጌዲዮን ቼክ ሪፐብሊክ የአውሮፓ ሕብረት አባልነቷንና በሕብረቱ ውስጥም የኢትዮጵያ ወዳጅ አገር መሆኗን በማንሳት፤ ወዳጅነቱን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባም በውይይቱ ላይ ተናግረዋል።

የቼክ ሪፐብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪያን ጁሬስካ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ፍሪያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቢዝነስ ልዑካን መርተው መምጣታቸውን በመግለጽም በቆይታቸው የኢትዮ-ቼክ ሪፐብሊክን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

ማሪያን ጁሬስካ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቁልፍ አጋራችን በመሆኗ ለግንኙነቱ ልዩ ትኩረት የምንሰጠው ነው ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም