ቀጥታ፡

ለሆስፒታል ግንባታ የተሰበሰበው ገንዘብ የታለመለትን ዓላማ ስቷል- የፌዴራል ዋና ኦዲተር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፦ ለወሎ ተርሸሪ ኬርና ቲቺንግ ሆስፒታል ግንባታ ህዝቡ ያዋጣው ገንዘብ የታለመለትን ዓላማ መሳቱን የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ።

የሆስፒታሉ የግንባታ ሂደትን አስመልክቶ ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስና የተሰበሰበው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ለማረጋገጥ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ መሰረት የተደረገው ኦዲት ለሆስፒታሉ ግንባታ ከህዝቡ የተሰበሰበው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ አለመዋሉን ተረጋግጧል።

በክዋኔ ኦዲቱም የፕሮጀክቱ ሥራ አመራር ቦርድ ዕዳ የመሰረዝ ሥልጣን ሳይኖረው ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳ መሰረዙ ማረጋገጥ ተችሏል።

የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ በአዲሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት በድጋሚ አለመመዝገቡም የኦዲት ሪፖርቱ አመላክቷል።


 

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ፤ ለሆስፒታሉ ግንባታ ከየክልሎቹ፣ በውጭ አገራት ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች በኩል ይሸጣል ተብሎ የተሰራጨ የብር ኩፖንን ጨምሮ ያልተመለሰ ቶምቦላ መኖሩን የኦዲት ግኝቱ አመላክቷል ብለዋል።

በአገር ውስጥ ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪና ብቁ፣ የማስተማር፣ የምርምርና የህክምና ማዕከል ለመገንባት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በየደረጃው ያዋጣው ገንዘብ ዓላማውን እንደሳተ ገልጸዋል።


 

የሆስፒታል የፕሮጀክት ሥራ አሥኪያጅ እሸቱ አየለ በበኩላቸው በአመራር ለውጥና በሌሎችም ምክንያቶች ሁሉንም ገንዘብ መሰብሰብ አለመቻሉን ተናግረዋል።

እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ግን ከህዝብ የተሰበሰበው ኃብት ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል ያደረጉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

የሥራ አመራር ቦርዱ ሰብሳቢ ጣይቱ ዓሊ ምዝገባውን አስመልክተው እንዳሉት በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ፍቃዱን ማደስ ያልተቻለው ሥራውን ወሎ ዩኒቨርሲቲ እንዲረከበው በመወሰኑ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ገንዘቡንም ሆነ ፕሮጀክቱን እንዲረከብ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ አለመስጠቱንም ጠቅሰዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጌትነት መላክ በበኩላቸው ፕሮጀክቱን ዩኒቨርስቲው እንዲረከበው ተደጋጋሚ ጥያቄ መቅረቡን አልሸሸጉም።

ይሁንና ዩኒቨርሲቲው በዋነኛነት ሲያቀርብ የነበረው ጥያቄ በገለልተኛ አካል የተጣራ የኦዲት ሪፖርት እንዲቀርብ ነው ብለዋል።


 

ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የተሰበሰበውን ገንዘብ መቀበል ተገቢ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ የሥራ አመራር ቦርዱ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ሥራውን ለወሎ ዩኒቨርሲቲ እንዲያስረክብ አቅጣጫ ቢቀመጥም ቦርዱ የክዋኔ ኦዲቱ እስከተካሄደበት ጊዜ ድረስ ለሥራ ማስኬጃ በሚል ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጪ አድርጓል።

ገንዘቡ ከህዝብ የተሰበሰበ በመሆኑ ሥራውን እንዲያስረክብ ከተወሰነ በኋላ መውጣት አልነበረበትም ሲሉም ስህተቱን ይፋ አድርገዋል።

የሥራ አመራር ቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ሚናስ ህሩይ (ዶ/ር) ግን የተሰበሰበው ገንዘብ አለመጥፋቱንና እንዲያውም ወለድ ጨምሮ ከነበረበት ከፍ ማለቱን ነው የገለጹት።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አረሬ ሞሲሳ፤ ቋሚ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቀጣይ ችግሩ የሚፈታበትን አቅጣጫ የሚያስቀምጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም