ኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውኃን ለማህበረሰብ ጥቅም ለማዋል የምታደርገውን ጥረት እንደግፋለን - የቼክ ሪፐብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ) ኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውኃን ለንጹህ መጠጥ ውሀ፣ ለግብርናና ኢንዱስትሪ ልማት ለማዋል የምታደርገውን ጥረት ሀገራቸው እንደምትደግፍ የቼክ ሪፐብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪያን ጁሪስካ ገለጹ።

ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ በውኃ ልማት ዘርፍ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1980ዎቹ ጀምሮ የተጠናከረ ትብብር እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት የቼክ ሪፐብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያን ጁሪስካ በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በውኃ ዘርፍ የተከናወኑ ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡


 

በጉብኝታቸውም በውኃና ሥነ ምድር ሃብት አጠቃቀም ዙሪያ 40 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በተመለከተ ገለፃ ተደርጎላቸዋል።

የቼክ ሪፐብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያን ጁሪስካ በሰጡት ማብራሪያ አዲስ አበባ ለሶስተኛ ጊዜ መምጣታቸውን አስታውሰው አሁን በተለየ ለውጥ ላይ መሆኗን አስተውያለሁ ብለዋል።

ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው፤ በተለይም በውኃ ልማት ዘርፍ ያላቸው ትብብር የላቀ መሆኑን አስታውሰዋል።

የውኃ ሀብት የግብርና፣ የኢንዱስትሪ ብሎም የህይወት መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታከናውናቸው ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ቼክ ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ በዘርፉ ለምታከናውናቸው ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ(/) ኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውኃን ለንጹህ መጠጥ እና ሌሎች ጥቅሞች እያዋለች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቼክ ሪፐብሊክ የልማት ኤጀንሲ በኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውኃ ሀብት ጥናት ከማድረግ ባለፈ ጥቅም ላይ እንዲውል እገዛ እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ማህበረሰቡ የከርሰ ምድር ውኃን ለመጠጥ እና ለመስኖ አገልግሎት እያዋለ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንንም በፋይናንስና በቴክኒክ እየደገፉ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም