ቀጥታ፡

በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል የሚደረግ የኃይል ትስስር በቀጣናው ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው - ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፦ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል የሚደረግ የኃይል ትስስር በቀጣናው ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።

የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር(East African Power Pool) የሚኒስትሮች ስብሰባ በኬንያ ሞምባሳ እየተካሄደ ነው።

በስብሰባው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል የሚደረግ የኃይል ትስስር በየሀገራቱ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በቀጣናው የሚፈጠረው የኃይል ትስስር የታዳሽ ኃይል ልማትን በስፋት ለማከናወንና በቀጣናው ዘላቂነት ያለው በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ ንጹህ ኢነርጂ ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ የኃይል ትስስር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።


 

በመድረኩ የተገኙት የዓለም ባንክና ሌሎች የልማት አጋር ድርጅቶች ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እያከናወነች የሚገኘው የኃይል ትስስር ለሌሎች አካባቢዎች ትልቅ ተሞክሮ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር(East African Power Pool) እ.አ.አ 2025 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ ተቋሙ ስራ ሙሉ በሙሉ እንደሚጀምር በአባል ሀገራት መካከል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ኢትዮጵያ ለጅቡቲ፣ ለኬንያ፣ እና ለሱዳን ኃይል እያቀረበች ሲሆን፤ በቀጣይም ለደቡብ ሱዳን እና ለታንዛንያ ኃይል ለማቅረብ በሂደት ላይ እንደምትገኝ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም