ቀጥታ፡

ሙስናን አምርሮ የሚጠላና የሚጠየፍ ትውልድ ለመገንባት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ

ደሴ/ወልዲያ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፡- ሙስናን አምርሮ የሚጠላና የሚጠየፍ ትውልድ ለመገንባት ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ። 

"ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ የፀረ ሙስና ትግል የነገን ስብዕና ይገነባል" በሚል መሪ ሀሳብ የፀረ ሙስና ቀን በደሴና ወልዲያ ከተሞች በፓናል ውይይት ዛሬ ተከብሯል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በወቅቱ እንዳሉት፤ ሙስና በአካባቢ ልማትና በህዝብ ጥቅም ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት መከላከል ጊዜ የሚሰጠው አይደለም።

ለዚህም በሥነ-ምግባር የታነፀና ሙስናን አምርሮ የሚጠየፍ ትውልድ በመገንባት ሁሉም በየደረጃው የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ከመሬት፣ አገልግሎት አሰጣጥና በሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ብልሹ አሰራሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ አጥፊዎችን ከህብረተሰቡ ጋር ለህግ እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡


 

ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረው፤ በከተማ አስተዳደሩ ለሙስና ተጋላጭ ጉዳዮችን በመለየት የመከላከል ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የደሴ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደምሴ ተፈራ በበኩላቸው እንዳመለከቱት፤ ሙስናን ከምንጩ ለማድረቅ ፊት ለፊት በድፍረት መታገል ይገባል፡፡

በገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ፣ በንግዱ፣ በመሬትና በሌሎች አገልግሎት ዘርፎች እየተስተዋለ ያለው ሙስና ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በህጋዊ ስርዓት መስራትና ህብረተሰቡን በፍትሃዊነት ማገልገል ይገባል ያሉት ደግሞ የፓናል ውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ፍሬህወይን ብርሃኔ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ በወልዲያ ከተማ በተከበረው የፀረ ሙስና ቀን በሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት የሥነ-ምግባር መኮንን አቶ ደሳለኝ ማዕረጉ እንደገለጹት፤ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት 529 የሙስና ጥቆማዎች መቅረባቸውን አስታውሰው፤ ከነዚህ ውስጥ በ352ቱ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፤ የ114ቱ ደግሞ ለህግ ተላልፏል ሲሉ አመልክተዋል።

ቀሪዎቹ በመጣራት ሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ሙስናን ቀድሞ በመከላከል ከ27 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ማዳን መቻሉን ጠቁመው፤ በሃራ፣ መርሳ፣ ሙጃና ላልይበላ ከተሞች ያለ አግባብ ለግለሰቦች ተላልፎ የተሰጠ 74 ሺህ 300 ካሬ ሜትር ቦታ መመለሱን አስረድተዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት  የቅሬታ ሰሚና የአስተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አለማየሁ ጋዲሳ፤ ሙስናና ብልሹ አሰራር ህብረተሰቡ የሚያነሳው   ችግር እንደሆነ ተናግረዋል።

ችግሩን ለመከላከል የተናጠል  ስራዎች በቂ ባለመሆናቸው ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ለዚህም ህዝብን በባለቤትነት ማሳተፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ታምራት ገብረስላሴ በሰጡት አስተያየት፤ ከነዳጅ አጠቃቀምና ከእቃ ግዥ ጀምሮ ከአግባብ ውጨ የሚባክነው የመንግስት ገንዘብ ወደ ትክክለኛ አሰራር እንዲመለሰ ትግል ወሳኝ ነው ብለዋል።

በፓናል ውይይቱ የከተማውና የዞኑ አመራር አባላትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም