ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሚድዋይፈሮች ማህበር በክልሉ የእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ ድጋፍ እየሰጠ ነው

አሶሳ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሚድዋይፈሮች ማህበር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በእናቶችና ህፃናት ጤና አጠባበቅ ላይ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሚድዋይፈሮች ማህበር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የስነ ተዋልዶ አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ በአሶሳ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ታረቀኝ ወዲ በወቅቱ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ሚድዋይፈሮች ማህበር በክልሉ በተለይም የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ያደረገ ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል።


 

ማህበሩ የእናቶች እና ህፃናት ጤና እንዲሻሻል በስፋት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ተወካዩ፤ ከእነዚህም አራት የተበላሹ አምቡላንሶች ተጠግነው ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ለአብነት አንስተዋል።

በሁለት ጤና ተቋማት ሙሉ ቁሳቁስ የተሟላለት የእናቶች ማቆያን በመገንባት ማህበሩ ለእናቶች ጤና መሻሻል አጋርነቱን አሳይቷልም ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ 23 የጤና ባለሙያዎችን በመቅጠር ለክልሉ የጤና አገልግሎት የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ሚድዋይፈሮች ማህበር ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ኢብራሂም ይመር በበኩላቸው ማህበሩ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች ላይ የእናቶች እና ህፃናትን ጤና ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በክልሉ እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ እና የህፃናት ደህንነት እንዲጠበቁ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሲሰጥ መቆየቱን ምክትል ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

የህክምና እና የጤና አገልግሎት ግብዓት በማሟላት እናቶች የተሟላ የጤናና ስነ ተዋልዶ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም