ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ ትብብራቸውን የሚያጠናክሩ የተለያዩ የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ ትብብራቸውን የሚያጠናክሩ የተለያዩ የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራረሙ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የቼክ ሪፐብሊክ አቻቸውን ማሪያን ዩሬችካን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማሳደግ እንደምትሰራ ገልጸዋል።

የቼክ ሪፐብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪያን ዩሬችካ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎችን አድንቀዋል፡፡

በተለይም የቼክ መንግሥት በቱሪዝም እና በዱር እንስሳት ጥበቃ ዙሪያ በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

ውይይቱን ተከትሎም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮቹ በተገኙበት የሀገራቱን የልማት እና የቱሪዝም ዘርፍ ትብብር ማጠናከር የሚያስችሉ የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈርመዋል።


 

የልማት ትብብር ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ ፈርመውታል።


 

የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት ለማስተዋወቅ ያለመውን የቱሪዝም ልማት ትብብር ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እና የቼክ ብሔራዊ ሙዚየም ዋና ዳይሬክር ሚሃል ሉኬሽ(ዶ/ር) ፈርመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም