የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የቺካጎ ኮንቬንሽን የተፈረመበት ቀን መታሰቢያ በተለያዩ ሁነቶች እያከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የቺካጎ ኮንቬንሽን የተፈረመበት ቀን መታሰቢያ በተለያዩ ሁነቶች እያከበረ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የቺካጎ ኮንቬንሽን የተፈረመበት ቀን መታሰቢያ በተለያዩ ሁነቶች እያከበረ ነው።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን 80ኛው ዓለም አቀፉ ሲቪል አቪየሽን ድርጅት የምስረታ በዓልና የቺካጎ ኮንቬንሽን የተፈረመበት ቀን መታሰቢያ እያከበረ ነው።
በበዓሉ ላይ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌታቸው መንግስቴ፣ የአለም አቀፉ ሲቪል አቪየሽን የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ጀኔራል ሉሲ ምቡጓ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
በዓሉ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም በአቪዬሽን ዘርፍ የተሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ፣ ሲምፖዚየም እና የፓናል ውይይት በማከናወን ይከበራል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌታቸው መንግስቴ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴክተር ለኢትዮጵያ ባህል፣ ቱሪዝም፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
የአቪየሺን ዘርፍ የአለም ህዝቦችን ትስስር ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልፀው ኢትዮጵያም ከዚሁ አንፃር ሚናዋን በላቀ መልኩ እየተወጣች መሆኑን አስረድተዋል።
በዓሉ በኢትዮጵያ መከበሩ በአቪዬሽን ዘርፍ የተሠማሩ ኩባንያዎችን ትብብር ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።