በደረሰኞች ላይ ልዩ መለያ ኮድ(QR-Code) አካቶ ማተም የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፦ የገቢዎች ሚኒስቴር እና ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት በደረሰኞች ላይ ልዩ መለያ ኮድ(QR-Code) አካቶ ማተም የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

የመግባቢያ ስምምነቱ ዓላማ ከታክስ ደረሰኝ ህትመት ጋር በተያያዘ ልዩ መለያ ኮድ(QR-Code) ተካቶ ማተም፤ የህትመት ጥያቄ መቀበል፣ ከታተመ በኋላ የስርጭት እና የቁጥጥር ሥርዓትን ማስፈን የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱን የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ እና የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ ፈርመውታል፡፡

በዚሁ ጊዜ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ ተቋሙ እንደሀገር ገቢን በብቃት ለመሰብስብ እና ሀገራዊ ወጪን በሀገራዊ ገቢ ለመሸፈን የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት ለግብር ከፋዩ የሚሰጡትን አገልግሎቶች ምቹ እና ቀልጣፋ ለማድረግ በርካታ ማሻሻያዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

ባለፉት ጊዜያት የማንዋል ደረሰኝ አስተዳደርን ውጤታማ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም የሀሰተኛ ደረሰኝ ህትመት መበራከት በግብር አሰባበሰቡ ላይ ፈተና ሆኖ ስለመቆየቱም ገልጸዋል፡፡

የታክስ ደረሰኝ አጠቃቀም እና አስተዳደርን ለማሻሻል የወጣ መመሪያ ቁጥር 188/2017ን አጽድቆ ስራ ላይ በማዋል ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ መልኩ እያንዳንዱ የደረሰኝ ቅጠል ሲታተም ልዩ መለያ ኮድ(unique QR code) ተካቶ እንዲታተም እና ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ከድርጅቱ ጋር በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

ደረሰኝ እንዲታተም ፍቃድ ከመስጠት ጀምሮ ያሉ አገልግሎቶችን ማስተናገድ እንዲቻል የራሱ የሆነ ዲጂታል ፕላትፎርም የተዘጋጀ ስለሆነ ደረሰኝ የሚያሳትም ማንኛውም ግብር ከፋይ በዚሁ መንገድ መስተናገድ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የማንዋል ደረሰኝ ተጠቃሚ የሆኑ ግብር ከፋዮች ከታህሳስ 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ የማንዋል ደረሰኝ የማሳተም ጥያቄያቸውን ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከየካቲት 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ብቻ የታተም የማንዋል ደረሰኝ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በበኩላቸው ድርጅቱ ደረጃውን የጠበቀ፣ ልዩ መለያ ኮድ (unique QR code) የተካተተበት እና አስመስሎ መስራት በማይቻል መልኩ የህትመት ሥራውን ለማከናወን በቂ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል፡፡

ድርጅቱም ይህን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት በተገባው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት መሰረት ለተግባራዊነቱ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም