ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መስኮች በትብብር ለመስራት እንደሚፈልጉ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መስኮች በትብብር ለመስራት እንደሚፈልጉ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መስኮች በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታወቁ።
ሶስተኛው የአፍሪካ ስታርታፕ ጉባኤ እና አውደ-ርዕይ በአልጄሪያ አልጀርስ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ከአልጄሪያ የዕውቀት ኢኮኖሚ፣ ስታርታፕ እና ማይክሮ ኢንተርፕራይዝ ሚኒስትር ኑረዲን ኡዳህ ጋር ተዋያይተዋል።
በውይይቱ ሁለቱ ተቋማት በኢኖቬሽን፣ በቴክኖሎጂ፣ በምርምር ፣ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ በመምከር በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ የስታርታፕ ስነምህዳር ላይ ሰፋፊ ስራዎችን በመስራት ሁሉም ዜጎች ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ስርዓት ግንባታ ላይ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም ዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ወሳኝ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች፣ ባለሀብቶች፣ ኢንቨስተሮች እና ከአለም አቀፍ አገሮች ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይ የተጀመረውን ስራ ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራም አመልክተዋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) የተመራው ቡድን በአልጄሪያ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ስታርታፕ ጉበኤ የሚኒስትሮች መድረክ ላይ በመሳተፍ በሳይንስቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ የኢትዮጵያን አቋም በማንፀባረቅ ላይ ይገኛል።
በኮንፈረንሱ ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሐመድ ቤልሆሲን፣ የአፍሪካ ሲቪል ማህበረሰብ ተወካይ፣ የግል ዘርፍ
ተወካዮች፣የአፍሪካ ሃገራት ሚኒስትሮች እና ተወካዮች መገኘታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።