የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር ተመርቆ ከካዛንቺስ በልማት ለተነሱ ነዋሪዎች ተላለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር ተመርቆ ከካዛንቺስ በልማት ለተነሱ ነዋሪዎች ተላለፈ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፦ የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደር ተመርቆ ከካዛንቺስ በልማት ለተነሱ ነዋሪዎች መተላለፉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ የገላን ጉራ የመኖሪያ እና የተቀናጀ የልማት መንደርን መርቀን ከካዛንቺስ በልማት ለተነሱ ነዋሪዎቻችን አስረክበናል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መልክ የሆነችው አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ ለማድረግ በገባነው ቃል መሰረት፣ መሰረተ ልማት ከማሟላት በተጨማሪ የሰው አኗኗርን ማሻሻል እና የነዋሪዎቻችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትልቅ ትኩረት ሰጥተን በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ነዋሪዎቻችንን ካረጀ እና ለመኖር ምቹ ካልሆነ የካዛንቺስ አካባቢ እንዲወጡ አድርገን ለኑሮ ምቹ የሆነ ቤት እና አካባቢ እንዲገቡ ያደረግን ሲሆን በዚህም የሰው ህይወትን የመቀየር ስራን ሰርተናል ሲሉም አክለዋል።
ከካዛንቺስ አካባቢ ለልማት በፈቃደኝነት የተነሳችሁ እና ከጎናችን የቆማችሁ ነዋሪዎችን ስለ ትዕግስታችሁ እና ድጋፋችሁ እያመሰገንኩ፣ ይህ ስራ እንዲሳካ ህግ እና አሰራሩን በመቀበል ቦታውን በፈቃደኝነት ለልማት የለቀቃችሁ የአካባቢው አርሶ አደሮችንም ላመሰግናቸው እወዳለሁ ብለዋል።
ይህን ታላቅ ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብታችሁ ያጠናቀቃችሁ ኮንትራክተሮችን፣ አማካሪ ድርጅቶችን፣ ድጋፍ ያደረጋችሁ አካላትን፣ ያስተባበራችሁ አመራሮችን እንዲሁም የክፍለ ከተማው አመራሮችን በራሳቸውና እና በከተማ አስተዳደሩ ስም አመስግነዋል።