ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ቀጣይነት ያለው ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል - አቶ ጌታሁን አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ቀጣይነት ያለው ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል - አቶ ጌታሁን አብዲሳ
አሶሳ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፦ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ቀጣይነት ያለው ትምህርት መስጠት እንደሚያስፈልግ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ ተናገሩ።
20ኛው የፀረ ሙስና ቀን "ወጣቶችን ያማከለ የፀረ ሙስና ትግል የነገን ሰብዕና ይገነባል" በሚል መሪ ሐሳብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ በፓናል ውይይትና በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ እንዳሉት ሙስናና እና ብልሹ አሰራር የሀገርን ኢኮኖሚ የሚጎዳ እና የመልካም አስተዳደር ችግርን የሚያስፋፋ ነው።
ይኸን ለማስቀረትም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማስፋት እና ቀጣይነት ያለው ትምህርት መስጠት እንደሚያስፈልግ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።
የትምህርት ተቋማት በመልካም ስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ በመፍጠር ረገድ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አቶ ጌታሁን ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ በበኩላቸው ውስብስብ እየሆነ የመጣውን ሙስና መታገል ሀገርን ማዳን ነው ብለዋል።
ተቋማት በመልካም ሥነ-ምግባር የታገዘ አገልግሎት በመስጠት ለፀረ ሙስና ትግሉ አጋዥ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ኮሚሽኑ በክልሉ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን እና ብልሹ አሰራሮች እንዲቀረፉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነም ገልጸዋል።
ወጣቶችን ያሳተፈ የፀረ ሙስና ትግል ለሀገር ዕድገት መሰረት ነው ያለው ደግሞ የኢትዮጵያ ወጣቶች ማህበር ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወጣት መሐመድ ሙሐሙድ ነው።
ሙስና ወጣቱን የሚያሸማቅቅ ነው ያለው ወጣት መሐመድ፤ በመሆኑም ሁሉም ሰው ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን መታገል አለበት ብሏል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ማህበር በመልካም ስነ ምግባር የታነፁ ወጣቶችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑንም አክሏል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት፣ የፍትህ አካላት፣ ወጣቶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።