የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች እየተተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፈጠረውን ምቹ ዕድል ተጠቅመው በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች እየተተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፈጠረውን ምቹ ዕድል ተጠቅመው በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017 (ኢዜአ)፦የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች እየተተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፈጠረውን ምቹ ዕድል ተጠቅመው በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮ-ቼክ ሪፐብሊክ የጋራ ቢዝነስን ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
የቼክ ሪፐብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያን ጁሬስካ በመድረኩ መክፈቻ ላይ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ውጤት ማስመዝገባቸውን በአዲስ አበባ ባደረጉት ጉብኝት ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በፎረሙ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ የተካሄደው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ አገራት መካከል አንዷ እንድትሆን ማድረጉን ገልጸዋል።
አምባሳደር ብርቱካን በቅርቡ የተካሄደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አሁን ላይ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል መፍጠሩን በመግለጽ የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ቼክ ሪፐብሊክ በግብርና ምርቶቾ ማቀነባበሪያ መሣሪያዎች ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ልምድ እና አቅም ያላት አገር እንደመሆኗ በዘርፉ ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገውን ትብብር እንደምታጠናክር ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን መዳረሻ ከሆኑ የአውሮፓ አገራት መካከል አንዷ ነች።
በቀጣይም የበለጠ የኢትዮጵያ ምርቶች እንዲገቡ ለማድረግ እንደሚሰራ አምባሳደር ብርቱካን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።