ኢትዮጵያ የስታርታፕ ስነ-ምህዳርን በማጎልበት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት እየሰራች ነው- ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የስታርታፕ ስነ-ምህዳርን በማጎልበት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት እየሰራች ነው- ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የስታርታፕ ስነ-ምህዳርን በማጎልበት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በትብብርና በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታው፥ በአልጄሪያ አልጀርስ ከተማ የኢትዮጵያ ስታርታፖች የተሳተፉበትን ሶስተኛውን የአፍሪካ ስታርታፕ ዓውደ ርዕይ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የአልጄሪያ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
አውደ ርዕይ የፈጠራ ባለሙያዎችን በማብዛትና ስታርታፖችን ወደ ግዙፍ ካንፓኒዎች በማሳደግ የዘርፉን የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) አፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችላትን የስታርታፕ ስነምህዳር ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን አውደ ርዕዩ የመጀመሪያው ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የፈጠራ ስራዎች አድገው ስታርታፕ በመሆን ከፍተኛ የስራ እድል ከመፍጠር አልፎ ዜጎች የሀብት ባለቤት እንዲሆኑ ማስቻሉን አመልክተዋል።
በጉብኝቱ የተስተዋሉት የስታርታፕ ስራዎች አፍሪካ ያላትን እምቅ አቅም ለኢኮኖሚ እድገቷ ዋነኛ ሞተር አድርጋ መጠቀም እንደሚያስችላት ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የስታርታፕ ስነ-ምህዳርን በማጎልበት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በትብብርና በትኩረት እየሰራች መሆኑንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።
በአልጀሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር መሐመድ፣ የአልጀሪያ የኖውሌጅ ኢኮኖሚ፣ የስታርታፖች እና ማይክሮ ኢንተርፕራይዞች ሚኒስትር ኑረዲን ኡዳህ፣ ከ45 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ሚኒስትሮችና ባለሀብቶች በአውደ ርዕዩ ጉብኝት ላይ መገኘታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።