ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲን ከሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ጋር አጣጥሞ መተግበር ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 30/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲን ከሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ጋር አጣጥሞ መተግበር እንደሚገባ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገለጹ።

የዜጎች ማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ክለሳ የተመለከተ ውይይት በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የፖሊሲ ክለሳው በትግበራ ወቅት የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ምክረ ሃሳቦች የሚሰጡበት እንደሆነ ተገልጿል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የኢትዮጵያ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ሁሉን አቀፍ ማህበረሰባዊ ለውጥ ለማምጣት ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ተፅዕኖ ፈጣሪ የማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞችን በመንደፍ እና በመተግበር ጉልህ እርምጃዎች እየወሰደ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ፖሊሲውን ከዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ወቅታዊ ክስተቶች ጋር እያጣጣሙ መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።

የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲውን ከረጅም ጊዜ የልማት እቅድ ጋር ማስተሳሰር፣ ድሃ ተኮር የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ፣ የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድ ማቋቋም፣ የመንግስት የአስተዳደር እርከኖችን ማቀናጀት እና የቢሮክራሲ መሰናክሎችን ማስወገድ የሚሉ ምክረ ሃሳቦች ቀርበዋል።

ፖሊሲው የተለያዩ ምክረ ሃሳቦችን በማካተት ክለሳ እንደሚደረግበት ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም