ቀጥታ፡

አገራዊ ምክክሩን የተሳካ ለማድረግ አባ ገዳዎችና የሃዳ ሲንቄዎች ሚና ከፍተኛ ነው -ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር 


አዳማ፤ህዳር 30/2017 (ኢዜአ)፡-አገራዊ ምክክሩን የተሳካ ለማድረግ አባ ገዳዎችና የሃዳ ሲንቄዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር ገለጹ።

ኮሚሽኑ  ከኦሮሚያ ክልል ከተወጣጡ አባገዳዎችና  ሃዳ ሲንቄዎች ጋር ቀጣይ በክልሉ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱን የተሳካ ለማድረግ በሚቻልበት ሂደት ላይ በአዳማ እየመከረ ይገኛል።

ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤በአገሪቷ የነበሩና አሁንም የሚስተዋሉ ያለመግባባት ችግሮችን በምክክር  እንዲፈቱ ኮሚሽኑ የማመቻቸት ስራዎችን እያከናወነ ነው።

በተለይም ባለፉት ጊዜያት የኮሚሽኑን ዓላማና ተልዕኮ ለህዝብ የማስገንዘብና የአጀንዳ ልየታ ስራ በአብዛኛው ክልሎችና  በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች መከናወኑን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱን በሶማሌ፣በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ  እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች መከናወኑንም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም በኦሮሚያ ክልል ከሰባት ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ታህሳስ 7/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ችግሮችን በምክክር ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማሳካት ህብረተሰቡ ወካይ አጀንዳዎችን እንዲያቀርብ ለማስቻል አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች ህዝቡን በማንቃትና በማስገንዘብ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል መድረኩ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።


 

በተለይም ተባባሪ አካላትን በመምረጥና የአጀንዳ ልየታ ስራን የተሳካ በማድረግ ረገድ ህዝቡን በማስተባበር አባ ገዳዎች እና ሃደ ሲንቄዎች የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

አምባሳደር መሐሙድ፤ የአሁኑ መድረኩም በክልሉ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱን የተሳካ ለማድረግ የትብብርና የማህበረሰብ መሪነት ሚናቸውን እንዲወጡ የተሰናዳ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም