ቀጥታ፡

በጅማ ከተማ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከተማዋን ውብና ምቹ እያደረጋት መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ

ጅማ፤ ህዳር 30/2017 (ኢዜአ)፡- የአካባቢውን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብት መሠረት ተደርጎ እየተሰራ ያለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ጅማ ከተማን ውብና ምቹ እያደረጋት መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ።

በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች እና አደባባዮች እየተሰራ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት በፍጥነት ለማጠናቀቅ   ቀንና ሌሊት በመሰራት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

በጅማ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የአካባቢውን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብት መሠረት ያደረገ በመሆኑ ከተማዋን ውብና ምቹ እያደረጋት መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገልጸዋል።


 

በተለይም የመተላለፊያ መንገዶቿ መስፋት እና የእግረኛና የተሽከርካሪ መተላለፊያ መለየቱ የትራፊክ አደጋን የሚያስቀርና በፍጥነት ለመንቀሳቀስም የተመቸ መሆኑን ተናግረዋል።

ጅማ በደቡብ ምዕራብ የአገሪቷ ክፍል ታሪካዊ ፣ የአካባቢው የንግድ መተላለፊያ እና በርካታ እንግዶች የሚስተናገዱባት ከተማ መሆኗን ነው ነዋሪዎቿ የሚናገሩት።

በመሆኑም ደረጃዋን የጠበቀች ከተማ እንድትሆን መሰል የኮሪደር ልማት መሰራቱ ተገቢ ነው ብለዋል።

ከነዋሪዎቿ መካከል አቶ ቢያ ጀማል "ጅማ የስሟን ያህል ውበትና ገጽታ እንድትላበስ የሚያስችል ልማት ላይ መሆኗን መገንዘብ ችያለሁ" ብለዋል።

በጅማ ከተማ እየተሰራ ያለው የኮሪደር ልማት ለከተማዋ  እድገትና ገጽታ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው በመሆኑም የሁላችንም ትብብር ያስፈልጋታል ብለዋል።

ጅማን ስናውቃት መንገዶቿ ጠባብ፤ በመሃል ከተማ ያሉ ቤቶቿ ያረጁ በመሆናቸው በገጽታዋ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ነበረው ሲሉ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ሃሊማ ሐሰን ናቸው።

ከተማዋ ከሌሎች ተጎራባች አካባቢዎች ጋር ያላትን የንግድና ማህበራዊ መስተጋብር መሠረት ያደረገ በመሆኑም ለምታስተናግዳቸው እንግዶቿም ጭምር  ይህ ልማት ያስፈልጋት ብለዋል።


 

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጣሃ ቀመር በበኩላቸው "ጅማ ከተማን ለማስዋብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የኮሪደር ልማቱን ቀንና ሌሊት እየሰራን ነው" ብለዋል።

የኮሪደር ልማት ስራው በፍጥነት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ከንቲባው፤ ለዚህም የከተማው ህብረተሰብ ለልማቱ ተባባሪና አጋዥ ሆኗል ብለዋል።

በኮሪደር ልማት ስራው በርካታ የስራ እድል መፈጠሩን ያነሱት  ከንቲባው፤ ጅማ ለኢንቨስትመንት እና ለጎብኝዎች ማራኪ ትሆን ዘንድ እየሰራን ነው ብለዋል።

የኮሪደር ልማቱ ምክንያት  የልማት ተነሺዎችም የሚገባቸውን የቤት መስሪያ ቦታና መጠለያ እንዲያገኙም እየተደረገ መሆኑን ከንቲባው ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም