በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የተሰማው ተኩስ የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ተሃድሶ ስልጠና በሚጓዙ የቀድሞ የኦነግ ታጣቂዎች የተሰማ ነው - ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የተሰማው ተኩስ የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ተሃድሶ ስልጠና በሚጓዙ የቀድሞ የኦነግ ታጣቂዎች የተሰማ ነው - ፖሊስ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አከባቢዎች የተሰማው የጦር መሣሪያ ድምፅ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ተሃድሶ ሥልጠና ማዕከላት በሚጓዙ የቀድሞ የኦነግ ታጣቂ ቡድን አባላት የተሰማ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
መንግሥት በሀገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች ታጥቀው ለሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ባቀረበው የሠላም ጥሪ መሠረት የኦነግ ታጣቂ ኃይል አባላት የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በስፋት እየገቡ መሆኑ ይታወቃል።
የታጣቂ ቡድኑ አባላትን ወደ ተዘጋጀላቸው የተሃድሶ ስልጠና ማዕከላት የማጓጓዝ ስራ በስኬት እየተከናወነ እንደሚገኝም ተገልጿል።
በዚህ መሀል ታጣቂዎቹ አዲስ አበባ ከተማን አቋርጠው ወደ ስልጠና ማዕከላት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት እየጨፈሩና የደስታ ስሜት እየገለጹ ሲንቀሳቀሱ የተኩስ ድምጽ በማሰማታቸው በከተማው ነዋሪ ህዝብ ላይ ድንጋጤና መረበሽ ሊፈጠር መቻሉን ፖሊስ ገልጿል።
ለተፈጠረው የዜጎች ድንጋጤና መረበሽ ይቅርታ የጠየቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ በቀጣይ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ከፍተኛ ጥንቃቄና የማስተካከያ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።