በትላንትናው እለት ያጋጠመውን የመብራት መቋረጥ ከሳይበር ጥቃት ጋር በማያያዝ አንዳንዶች ያሰራጩት መረጃ ሀሰተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትላንትናው እለት ያጋጠመውን የመብራት መቋረጥ ከሳይበር ጥቃት ጋር በማያያዝ አንዳንዶች ያሰራጩት መረጃ ሀሰተኛ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2017(ኢዜአ)፦በትላንትናው እለት ያጋጠመውን የመብራት መቋረጥ ከሳይበር ጥቃት ጋር በማያያዝ አንዳንዶች ያሰራጩት መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለኢዜአ እንዳረጋገጠው፣ ትላንት ያጋጠመው የመብራት መቋረጥ ችግር በንፋስ ምክንያት ባጋጠመ የተፈጥሮ አደጋ የኔትወርክ ማስተላለፊያ መስመር ላይ ችግር በመፈጠሩ የተከሰተ ነው።
በኔትወርክ የማስተላለፊያ መስመር ችግር ምክንያት ላጋጠመው የሃይል መቋረጥም ተቋሙ ተጠቃሚዎችን ይቅርታ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የሪል ታይም ግሪድ ኦፕሬሽን ማናጀር ኢንጂነር ጉልላት እንግዳ ለኢዜአ እንደገለፁት፣ ትናንት ምሽት አካባቢ ያጋጠመው የመብራት መቋረጥ ችግር ምክንያት ምስራቅ ወለጋ አካባቢ በሚገኝ ግዙፍ ኔትወርክ የማስተላለፊያ መስመር ላይ በንፋስ ሳቢያ የዛፎች መውደቅ በመከሰቱ በደረሰ ጉዳት ነው።
ይሁንና አንዳንዶች በተፈጥሮ ምክንያት ያጋጠመውን የመብራት መቋረጥ ከሳይበር ጥቃት ጋር በማያያዝ ያሰራጩት መረጃ ሀሰተኛና ሆን ተብሎ የተፈበረከ ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የሳይበር ጥቃትን መመከት የሚችል በጠንካራ አሰራር የታገዘ የመሰረተ ልማት ደህንነት ጥበቃ ያለው ስለመሆኑም አረጋግጧል።
በተቋሙ በኩል በተፈጥሮ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመከላከል የሃይል ማስተላለፊያ ታወሮች ከሚቆሙበት እስከ 30 ሜትር ድረስ ለእይታ ግልጽ እንዲሆኑ ያደርጋል።
የትላንቱ ችግር ግን ከዚህ እርቀት ውጪ የሆነና በወቅቱ በተከሰተ ከፍተኛ ነፋስ ምክንያት ትልልቅ ዛፎች በመውደቃቸው ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።
ከችግሩ ማጋጠም በኋላ ኔትወርኩን ወደነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ርብርብ ስለመደረጉ አስታውሰው በዚህም መስተካከል ችሏል ብለዋል።
በቀጣይ የሃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ያሉባቸውን አካባቢዎች ግልጽ የማድረግ ስራ ስለሚከናወን በየአካባቢው ያለው ህብረተሰብ ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ለሃይል መቋረጥ ምክንያት የሆኑ የታዎሮች ስርቆትን ለመከላከልም አጠቃላይ ህዝቡን ጨምሮ የከተማና የክልል ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።