ቀጥታ፡

19ኛው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበር በስኬት ተጠናቀቀ

አርባምንጭ፤ ህዳር 29/2017 (ኢዜአ)፦ አርባምንጭ ከተማ ያስተናገደችው 19ኛው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በደመቀ መልኩ መጠናቀቁን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስታወቀ፡፡

የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በሰጠው መግለጫ በዓሉ በድምቀትና በስኬት መጠናቀቁን አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሠናይት ሰለሞን እንደገለጹት 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ከኅዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቷል።


 

የባህል ሲምፖዚየምን ጨምሮ በመላ አገሪቷ የሚገኙ ዕሴቶችና ባህሎች ለእይታ የበቁበት ይኸው በዓል በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሮ በስኬት ተጠናቋል ብለዋል።

በዓሉ ላይ በክልሉ ያሉ ዕምቅ ኃብቶች ጎልተው እንዲወጡና እንዲታዩ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስሩ ይበልጥ እንዲጎለብት የሚያደርጉ ሥራዎች ተከናውነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች፣ የውጭና የአገር ውስጥ እንግዶች እንዲሁም የአገሪቷ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች በተገኙበት በስኬት ተከብሯል።


 

የዘንድሮ በዓልን ያስተናገደው የደቡብ ክልል ቀጣዩን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን እንዲያከብር ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስረክቧል።

በዓሉ በስኬት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የፌዴራልና የክልሎች ባለድርሻ አካላት፣ የአርባምንጭ ከተማና አከባቢዋ ነዋሪዎች እንዲሁም የጸጥታና ባለድርሻ አካላት ላበረከቱት አስተዋፅኦም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም