የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ስናከብር የኢትዮጵያን ቀለመ ብዙ ማንነት፣ እሴትና ፀጋ በማውሳት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2017(ኢዜአ)፦ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን "ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ ስናከብር የኢትዮጵያን ቀለመ ብዙ ማንነት፣ እሴትና ፀጋ በማውሳት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለ19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡


 

የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ይቀርባል፦

እንኳን ለ19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አደረሳችሁ!

ኢትዮጵያ ማለት ኅብር ናት፡፡ አንድነት የሚገለጥባት ድንቅ ምድር ናት። የብሔር ብሔረሰቦች ኅብር አንድነቷን አይሸረሽረውም፤ ሀገራዊ አንድነቷ ኅብራዊነቷን አይጠቀልለውም። ሁለቱም ያስፈልጓታል። ኅብራዊነቷ ጌጧ፣ መልኳ፣ ጸጋዋ፣ ሀብቷ ነው። አንድነቷ ደግሞ ኃይሏ፣ ጉልበቷ፣ ዐቅሟ ነው።

የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን "ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ ስናከብር የኢትዮጵያን ቀለመ ብዙ ማንነት፣ እሴትና ፀጋ በማውሳት ነው። ምን ያህል የተሣሠርን፣ የተዛመድን፣ የተጋመድንና የተወራረስን እንደሆን እንማርበታለን። ይሄን ሁሉ ሀብት፣ ጸጋና ዕድል አውጥተን ለብልጽግና ከተጠቀምንበት የሚያደናቅፈን ዕንቅፋት ፣ የሚያሰናክለን ወልጋዳ እንደማይኖር እናረጋግጥበታለን።

ሆኖም ዛሬም ድረስ ያልተሻገርናቸው ከትናንት የተሻገሩ ዕዳዎች፣ ነጠላ ትርክት የወለደው የፖለቲካ ስብራት እንዲሁም ድህነት የሀገራችንን የከፍታ ጉዞ ወደ ኋላ ጎትተዋል። እነዚህን ሳንካዎች በማለፍ የበለፀገች፣ ጠንካራና የታፈረች ህብረ ብሔራዊት ሀገር ለመገንባት በጋራ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይገባናል።

በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ እምቅ ጥበብ፣ እውቀት፣ ሀገር አሻጋሪ ሀሳቦችና ባህሎች አሉ። እነዚህን እሴቶች በመደመር ለሀገር የከፍታ ጉዞ እና ለጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠቀም ያስፈልጋል።

መግባባት ስንፈጥር የተደመረ አቅም ይኖረናል፤ ይህ ደግሞ ከልዩነት ፖለቲካ ወደ አንድነት ከድህነት ወደ ብልፅግና የምናደርገውን ጉዞ ያፋጥናል።

ለሁላችንም መልካም በዓል ይሁንልን!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም