የሰላምን መንገድ መርጠው የመጡ ታጣቂዎችን ፈለግ ሌሎችም ሊከተሉ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሰላምን መንገድ መርጠው የመጡ ታጣቂዎችን ፈለግ ሌሎችም ሊከተሉ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2017(ኢዜአ)፦ ከጦርነትና መገዳደል ይልቅ የሰላምን መንገድ መርጠው የመጡ ታጣቂዎችን ፈለግ ሌሎችም ተከትለው እንዲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በአርባምንጭ ከተማ በደማቅ ስነ-ስርአት ተከብሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ እንደ አንድ ትልቅ ቤተ-መፅሃፍት በመሆኗ ኢትዮጵያን ለማወቅ ብሔሮች ብሔረሰቦችን ማጥናት፣ ማወቅና መማር ያስፈልጋል ብለዋል።
በመሆኑም በመደመር እሳቤ በህብረ-ብሔራዊነትና በጋራ ትርክት ልባችንን ወደ ሰላምና ፍቅር በመመለስ ኢትዮጵያን ማበልጸግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ከጦርነት ሰላም ይሻላል ብለው በሺህዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላምን መንገድ መርጠው መጥተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌሎችም ይህንን ፈለግ ተከትለው እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ አባይ ተደምረን በህብረ-ብሄራዊ አንድነት ሰላምን በማስቀደም የማያልፍ ታሪክና አሻራችንን እናሳርፍ ብለዋል።
የጠብ፣ የጥላቻና የውጊያ ትጥቅ በመፍታት ፍቅርና ሰላምን እንታጠቅ ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚረጋገጠው በመደመርና በስራ ትጋት በመሆኑ ሰላምን በማስቀደም በህብረ-ብሄራዊነት በጋራ እንቁም በማለትም ጥሪ አቅርበዋል።