ሀገራዊ ለውጡ ወደ ዕውነተኛ ፌዴራሊዝም ያሻገረ ነው - አቶ ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡ ወደ ዕውነተኛ ፌዴራሊዝም ያሻገረ ነው - አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2017(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ለውጡ ወደ ዕውነተኛ ፌዴራሊዝም ያሻገረ መሆኑን የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በአርባ ምንጭ ከተማ በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ነው።
በዓሉ "ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ኃሳብ ነው እየተከበረ የሚገኘው።
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል የፍቅር ምንጭና የአንድነት መሰረት መሆን ችሏል።
የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በአርባ ምንጭ ከተማ የሩቅና የቅርብ ጠላቶችን ተስፋ በሚያስቆረጥ መልኩ በድምቀት እየተከበረ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ውበትና ፀጋ የሚታደሉት እንጂ የሚታገሉት እንዳልሆነም ገልጸዋል።
ብልፅግና ፈተናዎችን አልፎ ተስፋ ያላትና አስተማማኝ ሀገር እንድትሆን አስችሏል ነው ያሉት።
ሀገራዊ ለውጡ ከይስሙላ ፌዴራሊዝም ወደ ዕውነተኛ ፌዴራሊዝም ያሸጋገረ እንዲሁም ነጠላ ትርክትን ወደ ብሔራዊ ትርክት በመቀየር ትሩፋት ነበረው ብለዋል።
ወደ ብልፅግና ያሻገሩ ፈተናዎችን ወደ ኃይል ለለወጡት፣ የሀሳብ አፍላቂና የለውጡ ፋና ወጊ ለሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ምስጋና ችረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኢትዮጵያ ተምሳሌት ነው ያሉት አቶ ጥላሁን፣ ክልሉ በተፈጥሮና በባህል የታደለ በመሆኑ ለሀገር የሚበጅ ምርታማነትን ያረጋግጣል ሲሉ ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር እና ትብብርን ማጎልበት እንደሚገባ ነው የገለጹት።