ቀጥታ፡

የወል ዕውነት ለመገንባትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር መስራት ይገባል - አቶ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 29/2017(ኢዜአ)፦ የወል ዕውነት ለመገንባትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር መስራት ይገባል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።

በ19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በአርባ ምንጭ ከተማ በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ኃሳብ ነው እየተከበረ የሚገኘው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አከባበር ላይ እንዳሉት፥ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጤናማ የፌዴራሊዝም ስርዓት እንዲፈጠር እየሰራ ይገኛል።

ባለፉት 18 ዓመታት የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል መከበሩ የሕገ መንግስት ወሳኝ አስተምህሮ የመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

በዓሉ ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ ለሕብረ ብሔራዊነት አስተዳደር እንዲሁም ለህገ መንግስት አስተምህሮ መሰረት የጣለ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በተለይም ከለውጡ በኋላ ከልዩነት ይልቅ አንድነት እንዲጎለብት የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የብዝሀ ማንነት መገኛ መሆኗን ተከትሎ ሁሉንም በእኩልነት ለማስተናገድ አስቻይ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምክክር እየተደረገ ባለበት እንዲሁም የደቡብ ክልል ምስረታዎችን በማረጋገጥ የለውጡን ትሩፋቶች እየተቋደስን ባለንበት ወቅት በዓሉ መከበሩ ለየት እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል።

የፌዴራሊዝም ስርዓት ለብዝሀ ማንነት ወሳኝ በመሆኑ መንግስት ይህንኑ ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የሀገረ መንግስትና የብሔረ መንግስት ክፍተቶችን በማረም ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የነበረውን የማህበራዊ ግንኙነት መዛባት በመመለስ የተዛባ ትርክትን ለማረም የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ አስታውቀዋል፡፡

የወል ዕውነት ለመገንባትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር መስራት ይገባል ነው ያሉት።

ለኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የጋራ ሕልውና እና አብሮነት ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የዘንድሮው መሪ ቃል ትኩረት ከዚህ የመነጨ መሆኑንም አፈ ጉባኤው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም