ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል የሚከበረው የእርስ በርስ ግንኙነትን ይበልጥ በማጠናከር ነው - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

አርባምንጭ፤ ህዳር 28/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል የሚከበረው የእርስ በርስ ግንኙነትን ይበልጥ በማጠናከር ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን "ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ አርባምንጭ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።

በዓሉ በስኬት እንዲከበር ላቅ ያለ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም ለመገናኛ ብዙሀን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እውቅና ሰጥቷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ እውቅና ከተሰጣቸው የመገናኛ ብዙሃን መካከል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ይገኝበታል።


 

በዚህ መርሀ ግብር ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፣ የክልሎች ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎችን ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራር አባላት ተገኝተዋል።

ጥሪ የተደረገላቸው አምባሳደሮች፣ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወካዮች፣ አባገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ተወካዮችም ታድመዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ያካሄዱትን መራራ ትግል ተከትሎ በተቀዳጁት ድል ያረቀቁትን ህገ መንግስት ያፀደቁበት ልዩ ዕለት ነው።


 

የ19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን የሚከበረው የእርስ በርስ ግንኙነትን ይበልጥ በማጠናከር መሆኑን አመልክተዋል።

የህዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ ለሚገኘው ስኬት ትልቅ ድርሻ አለው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ልዩነት ውበት መሆኑን አብራርተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚያዝያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም ባካሔደው ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው ሕገ-መንግሥቱ የጸደቀበት ኅዳር 29 የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ተብሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲከበር መወሰኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም