ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ፈጣን እድገት የሚመጥን የሰው ኃብት ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 28/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ፈጣን እድገት የሚመጥን የሰው ኃብት ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የአቪዬሽን የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 450 የአቪዬሽን ሙያተኞች ዛሬ አስመርቋል።

ከተመራቂዎች መካከል 115 የአውሮፕላን አብራሪዎች፤ 123 የበረራ መስተንግዶ፤ 84 የጥገና ዘርፍና 128 የኮሜርሻል ዘርፍ ሙያተኞች መሆናቸው ተገልጿል።


 

የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ካሴ ይማም በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው የሰለጠነ የሰው ኃብት በማፍራት ለአየር መንገዱ እድገት የራሱን ሚና እየተወጣ ነው።

በዚህም የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲው፣ በየዓመቱ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት ለሚመጡ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህንንም ተከትሎ በዛሬው ዕለትም በዩኒቨርሲቲው የተመረቁት 450 የተለያዩ ሙያተኞች ለዘርፉ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ነው ያስረዱት።

በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የአየር መንገዱን ፈጣን እድገት የሚመጥን የሰው ኃብት በጥራትና በብቃት የማፍራት ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

የማዕረግ ተመራቂና የዋንጫ ተሸላሚ ካፕቴን ጸደንያ ሞገስ፤ የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድን መቀላቀሏ እንዳስደሰታት ተናግራለች።

በሙያዋም ሀገሯን በሙሉ አቅሟ በማገልገል የአየር መንገዱን መልካም ሥምና ዝና ለማስቀጠል ያላትን ቁርጠኝነትም አስረድታለች።


 

ሌላኛው የማዕረግ ተመራቂና የዋንጫ ተሸላሚ ካፕቴን ልዑል ማሙዬ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስኬት ለማስቀጠል እሰራለሁ ብሏል።

ሰልጣኞቹ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትና ከሌሎች የተለያዩ አህጉራት የተውጣጡ መሆናቸውም ተገልጿል።

በመርኃ ግብሩ የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም