ቀጥታ፡

ማህበሩ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ድጋፍ እያደረገ ነው

መቀሌ፤ ህዳር 28/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የሚድዋይፈሪ ማህበር በትግራይ ክልል ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ  ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ማዘንጊያ ገለጹ።

ማህበሩ የሚሰጠውን የስነ ተዋልዶ አገልግሎት ፕሮጀክት አፈጻጸምን አስመልክቶ ዛሬ በመቀሌ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በዚህ ወቅት፥ ማህበሩ ከባለድርሻ ጋር መተባበር ባለፉት ዓመታት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ እናቶች እና ህፃናት የጤና አገልግሎት መስጠቱን አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል የስነ ተዋልዶ ትምህርት በማጠናከር፣ስልጠና በመስጠት እና የባለሙያዎች ቅጥር በመፈፀም አገልግሎቱን እያጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም  ባለፉት ሶስት ዓመታት በትግራይ ክልል አገልግሎቱን ለማጠናከር 151 የሚድዋይፈሪ ባለሙያዎችን ቀጥሯል ብለዋል።

እናቶች በቅድመ ወሊድ፣ ወሊድና ድህረ ወሊድ የጤና አገልግሎት የሚያገኙባቸው 68 የማቆያ ማዕከላት የአገልግሎት መኖራቸውብም አቶ ፍቃዱ አመላክተዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ ተወካይ አቶ ገብረሀወርያ ገብረክርስቶስ በበኩላቸው፤ ማህበሩ የእናቶች እና ህፃናት የጤና አገልግሎት እንዲጠናከር ድጋፍ እያደረገ ነው።

በኢትዮጵያ ሚድዋይፈሪ ማህበር የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ሲስተር አበባ ሓዱሽ ፣ በክልሉ በአሁኑ ወቅት ከ1 ሺህ 600 በላይ የሚድዋይፈሪ ባለሙያዎች ሙያዊ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሚድዋይፈሪ ማህበር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በትግራይ፣በአማራ፣ኦሮሚያ፣በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች “በችግር ጊዜ የስነ ተዋልዶ አገልግሎት” የተባለ ፕሮጀክት ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም