የሀገረ መንግሥት ግንባታውን ውጤታማ ለማድረግ ሀገራዊ መግባባት ላይ አበክሮ መሥራት ይገባል - አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የሀገረ መንግሥት ግንባታውን ውጤታማ ለማድረግ ሀገራዊ መግባባት ላይ አበክሮ መሥራት ይገባል - አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፤ ህዳር 28/2017(ኢዜአ)፦ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ስኬታማነት ሀገራዊ መግባባት ላይ አበክሮ መሥራት ይገባል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
በ19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ዋዜማ በአርባ ምንጭ ከተማ ሲምፖዚየም ተካሂዷል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የዘንድሮው በዓል ልዩ የሚያደርገው በሁሉም መስኮች እመርታዎች የተመዘገቡበት ወቅት በመሆኑ ነው።
በዓሉ የሕዝቦች ባህላዊ እሴቶች፣ ማንነትን ያከበረ ሕብረ ብሔራዊና ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጠናከር እንዲሁም ሀገራዊ መግባባት እንዲጎለብት ያግዛል ብለዋል።
ቀኑ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች ሲከበር አንድነት እንዲጎለብት፣ ሕገ-መንግሥቱና በፌደራል ሥርዓት ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ 19ኛው በዓልም ''ሀገራዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ኃሳብ ከሕዳር አንድ ቀን ጀምሮ ሲዘከር መቆየቱን ተናግረዋል።
በዓሉ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን መሰረት ያደረገ ሀገራዊ መግባባት እንዲጎለብት የማይተካ ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል።
ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ስኬታማነት ደግሞ ሀገራዊ መግባባት ላይ አበክሮ መሥራት ይገባል ብለዋል።
በፌደራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ከራስ አስተዳደር ባሻገር የበይነ መንግሥታት ግንኙነትም ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው፤ ይህ ደግሞ መተባበር፣ መተሳሰብ፣ አብሮነት፣ ፍትኃዊነትና እኩልነት እንዲጠናከር ያግዛል ነው ያሉት።
ሀገራዊ ሰላምን በማረጋገጥና ፍትኃዊነትን በማስፈን ኢኮኖሚያዊ የጋራ ተጠቃሚነት ማሳደግ ለሀገራዊ መንግሥት ግንባታ አይተኬ ሚና እንዳለውም አንስተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፀሐይ ወራሳ በበኩላቸው በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የማንነት ዕውቅና የሰጠና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አክብሮ ለማስቀጠል ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያውያን ብዝኃነትንና የአንድነትን መሰረት ያደረጉ እንዲሁም በቋንቋ፣ በታሪክ፣ በባህል የተሳሰርን ወንድማማች ሕዝቦች ነን ብለዋል።
በዓሉም የአብሮነትና የመከባበር እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር በእኩልነት የምንኖርበት ሀገር ለመገንባት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በሀገራዊ ለውጡ የተመዘገቡ ድሎችንና የብልጽግና ጉዞን ለማስቀጠል ብሔራዊ ትርክት ግንባታን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ብዝኃነት የሀገራችን ውበት ጥንካሬ ምንጭ በመሆኑ አንድነትንና ወንድማማችነትን በማጎልበት ሀገርን ወደ አዲስ የብልጽግና ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በዓሉም ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የሚጠናከርበትና ባህልና እሴቶች በአደባባይ የምናሳይበት እንዲሁም የውበት ማድመቂያና የቱሪዝም መሰረት የሚሆን ነው ብለዋል።