ኤች አይ ቪ/ኤድስንና ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ኤች አይ ቪ/ኤድስንና ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 28/2017(ኢዜአ)፦ ኤች አይ ቪ/ኤድስንና ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል መገናኛ ብዙሃን የማህበረሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ሥራዎች ላይ ይበልጥ አተኩረው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) የፀረ-ፆታዊ ጥቃት፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስና የፀረ-ሙስና ቀናትን አስመልክቶ የፓናል ውይይት አካሂዷል።
በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በከተማው የኤች አይ ቪ ሥርጭትን ለመከላከል በተደረገው ርብርብ በቫይረሱ የመያዝና የመሞት ምጣኔን መቀነስ ተችሏል።
በዚህ ሂደት ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰው አሁንም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የድርሻቸውን አጠናክረው ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት በፌዴራል ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የስነምግባር ግንባታና የፀረ-ሙስና ባለድርሻ አካላት መሪ ስራ አስፈፃሚ ከፍያለሁ አለሙ በበኩላቸው የእድገት ፀር የሆነውን ሙስናን ለመከላከል እና ለማጋለጥ መገናኛ ብዙሃን በምርመራ ዘገባ ላይ የተሻለ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በዕለት ተዕለት የዘገባ ስራዎቻቸው ሙስናን መከላከልና ማህበረሰቡን ማንቃት ላይ አተኩረው መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ለሀገር እድገትና ብልፅግና እንቅፋት የሆኑት ሙስና፣ ኤች አይ ቪ/ኤድስና ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከል የጋራ ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልግ የገለፁት ደግሞ የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነጋሲ አምባዬ ናቸው።
መገናኛ ብዙሃን የሀገር ልማትና ብልፅግና እንዲረጋገጥ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ መስራት እንዳለባቸውም ገልፀዋል።
የተቋሙ የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክተር ታደለች ቦጋለ ተቋሙ የሴቶችን ጥቃት ለመከላከልና የኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመግታት የሚያግዙ የዘገባ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም መሰል ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና መገናኛ ብዙሃን ሙስናና ሌሎች የማህበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት በዘገባዎቻቸው አተኩረው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።