ቀጥታ፡

 በሥነ- ምግባር የታነፀ ትውልድን ለመገንባት ሚናችንን እንወጣለን - የሃይማኖት አባቶች

ባህርዳር፤ህዳር 28/2017 (ኢዜአ) ፡-ሙስናን የሚጠየፍና በሥነ- ምግባር የታነፀ ትውልድን ለመገንባት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ በአማራ ክልል የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።

"ስነ-ምግባርን በመገንባትና ሙስናን በመከላከል ረገድ የሃይማኖት ተቋማት ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ የሃይማኖት አባቶችን ያሳተፈ የምክክር መድረክ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተካሂዷል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባህርዳር ሀገረ ስብከት ዋና ፀሐፊ መላከ ብርሃን ፍስሃ ጥላሁን በመድረኩ እንዳመለከቱት፤ ቤተክርስቲያኗ ለምእመኗ የምትሰጠው ስነምግባርን የሚያንጽ ትምህርት ቀጥላበታለች።

ሀገር ማለት ትውልድ ነው፤ትውልድ ማለት ደግሞ ሀገርን የመገንባት አቅም ያለው የሰው ሃይል መሆኑን በመገንዘ
ብ ትውልዱን በስነ ምግባርና በግብረ ገብነት በማነጽ ላይ አተኩረን መስራት ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል።

መልካም ስነ ምግባር ያለው ትውልድ ለመፍጠር ቤተክርስቲያኗ ተግታ ታስተምራለች ብለዋል።

በባህርዳር ከተማ የሰላም በር መስጂድ አሰጋጅ ሼህ መሀመድ አብራር በበኩላቸው፤የእምነቱ ተከታዮች ሃይማኖታዊ አስተምሮውን እንዲገነዘቡ ከማድረግ ባሻገር መልካም ስነምግባር እንዲላበሱ የማስተማሩ ተግባር መቀጠሉን ተናግረዋል።

የራሱ ያልሆነን ገንዘብ ትውልዱ እንዲጠየፍና ብልሹ አሰራርን እንዲታገል አባታዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ራሳችን ከሙስና በመጠበቅ አርአያ ሆነን ሌለውን ለማስተማር ጥረት እያደረግን ነው ያሉት ደግሞ የሰሜን ምዕራብ የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ዋና ፀሐፊ መጋቤ ገብሬ አሰፋ ናቸው።

ያላቸውን ለሌላቸው እንዲያካፍሉ እንጂ የእነሱ ያልሆነውን መውሰድ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ መሆኑን ለዕምነቱ ተከታዮች ማስተማራቸውን እንደሚቀጠሉ ተናግረዋል።

የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃብታሙ ሞገስ በበኩላቸው እንዳሉት ፤ ሙስናና ብልሹ አሰራርን በዘላቂነት መከላከል የሚቻለው በየደረጃው በሥነ- ምግባር የታነፀ ትውልድ መገንባት ሲቻል ነው።


ሙስናን የሚጠየፍና በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመገንባት መንግስት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም የሃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በምክክር መድረኩ የኦርቶዶክስ፣ የእስልምና፣ የካቶሊክና የፕሮቲስታንት እምነት ተቋማት አባቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም