ቀጥታ፡

በዓሉ መከበሩ በመካከላችን አብሮነትና መቻቻል እንዲጎለበት ያደርጋል - የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

ሰመራ፤ ህዳር 28/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል መከበር በመካከላቸው አብሮነትና መቻቻል እንዲጎለብት እንደሚያደርግ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ።

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ''አገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በሰመራ ዮኒቨርሲቲ ተከብሯል።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሰመራ ዮኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች በዓሉ አብሮነትና መቻቻልን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

ከአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ የመጣው ተማሪ አብዱ መሐመድ፤ በዓሉ አብሮነታችን እንዲጨምር አድርጓል ይላል።


 

ትንሿ ኢትዮጵያ ተብለው የሚገለፁት ዮኒቨርሲቲዎች ውስጥ በዓሉ መከበሩ አብሮነት፣ አንድነትና መቻቻል እንዲጎለብት ያደርጋል ሲልም ተናግሯል።

ከሀረሪ ክልል የመጣችው አንሻ ኢድሪስ በበኩሏ በዓሉን በጋራ ተሰባስበን ስናከብር አብሮነታችን እየጠነከረ፤ የጋራ ማንነቶቻችን ጎልተው እንዲታዩ ያደርጋል ብላለች።


 

በፍቅርና በአንድነት አምረንና ተውበን በዓሉን ማክበር ችለናል ያለችው ደግሞ ከአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የመጣችው ተማሪ ፋይዛ መሐመድ ናት።

ከወላይታ ዞን የመጣው ተማሪ ተሻለ አዳሙ፤ በዓሉን በጋራ ሰናከብር አንድነታችንን በማንፀባረቅ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ ብሏል።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ሁሴን ኡመር(ዶ/ር) እንዳሉት በዓሉን በጋራ ማክበር የባህል፣ ወግና ብዝሃ ውበቶች ጎልተው እንዲወጡ ዕድል የፈጠረ ነው።

በዓሉ በልዩነት ውስጥ ያለው አንድነት የጥንካሬያችን መገለጫ እንዲሆን የሚያሳይ ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ በዓሉ በዩኒቨርሲቲው መከበሩም በተማሪዎች መካከል ያለውን ትስስር ያጠናክራል ነው ያሉት።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ በሰላም አምባሳደርነቱ የሚታወቅ መሆኑን የገለፁት ምክትል ፕሬዚዳንቱ በዓሉ በዩኒቨርሲቲው ያለውን አብሮነት፣ መከባበርና አንድነት ለማስቀጠል ያግዛል ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም