በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል በተሟላ ሁኔታ ለማቅረብ የባለድርሻ ተቋማት ትብብር ማጠናከር ይገባል- ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል በተሟላ ሁኔታ ለማቅረብ የባለድርሻ ተቋማት ትብብር ማጠናከር ይገባል- ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ህዳር 28/2017 (ኢዜአ)፦በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል በተሟላ ሁኔታ ለማቅረብ የባለድርሻ ተቋማት ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኮርፖሬሽኑ አመራሮች ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በልዩ የኢኮኖሚ ዞን ያለውን የኃይል አቅርቦት በተሟላ ሁኔታ ማቅረብ በሚቻልባቸው ሁኔታና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታት ያለመ ነው።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገቡ ባለሃብቶች ስራቸውን በስኬት ለማከወንና ወደ ዞኖቹ ለመግባትም የኃይል አቅርቦት ጉዳይ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ከሁለቱ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ተግዳሮቶች ሲያጋጥሙም በፍጥነት መልስ መስጠት መቻሉ የሚበረታታና ትብብሩን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመላው ሃገሪቱ በሚገኙት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጣና የኃይል አቅርቦቱን በተሟላ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ወደፊትም የሃገርን ልማት ለማረጋገጥ በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡
በልዩ የኢኮኖሚ ዞን በተሟላ ሁኔታ አቅርቦቱን ለማሳደግና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታት የሚያስችል ከሶስቱ ተቋማት የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሯል ሲል ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።