ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአል አንድነት እንዲጸናና ዘርፈ ብዙ ድል እንዲመዘገብ መሰረት የጣለ ነው -አቶ አገኘሁ ተሻገር

አርባ ምንጭ፤ህዳር 28/2017 (ኢዜአ)፦የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአል አንድነት እንዲጸናና ዘርፈ ብዙ ድል እንዲመዘገብ መሰረት መጣሉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።

የዘንድሮውን የብሔሮች፣ብሔረሰቦች ቀን በማስመልከት በአርባምንጭ ከተማ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት አፈ ጉባኤ አገኘሁ፥ ባለፉት 18 ዓመታት በኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች አስተናጋጅነት በዓሉ ሲከበር መቆየቱንም አስታውሰዋል።


 

በዓሉ የሚከበረው ሕዝቦች እሴቶቻቸውን፣ልምዶቻቸውንና ባህሎቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ታልሞ መሆኑን አንስተው፥ይህም ህብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም፣ለፈጣን ልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲነሳሱ ለማድረግ ነው ብለዋል።

እንዲሁም በሕገ መንግሥቱና በፌዴራል ሥርዓቱ ዙሪያ የዜጎችን ግንዛቤ በማጎልበት አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ማስቻል ጭምር መሆኑን አስታውሰዋል።

በዓሉ ሕዝቦች ለረዥም ዘመናት ይዘውት የቆዩትን አብሮነት እንዲያጎለብቱ፣ከልዩነት ይልቅ አንድነትን እንዲያፀኑ እና በሕገ መንግሥቱና በፌዴራል ሥርዓቱ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲፈጠሩ የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።

አፈ ጉባኤው አክለውም፥ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን መሠረት ያደረገ አገራዊ መግባባት ለአገረ መንግሥት ግንባታችን የማዕዘን ድንጋይ ነው ብለዋል።

አሁን የተጀመረው የአገረ መንግሥት ግንባታ እንዲሳካ መትጋት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

በአገራችን የተገኙትን ሕገ መንግሥታዊ ድሎች እና ውጤቶች ጠብቀን ተጨማሪ ድሎችን ለማስመዝገብ በሚደረገው ሕዝባዊ ተሳትፎና እንቅስቃሴ ላይ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

አፈ-ጉባኤ አገኘሁ በንግግራቸው፥ ሁሉም የአገርን ሰላም በመጠበቅና በልማት ሥራዎች ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የአገር ብልጽግና እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም