የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በጥሩ ሂደት እየተከናወነ መሆኑን በምልከታ አረጋግጠናል - የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች - ኢዜአ አማርኛ
የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በጥሩ ሂደት እየተከናወነ መሆኑን በምልከታ አረጋግጠናል - የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 28/2017(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በጥሩ ሂደት እየተከናወነ መሆኑን በምልከታቸው እንዳረጋገጡ የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች ገለጹ።
የአፍሪካ ሕብረት፣ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽንና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችና ተወካዮች በዕዳጋ-ሀሙስና በመቀሌ ማዕከል የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሀድሶ ሥልጠና አሰጣጥ ሂደት ተመልክተዋል።
በአፍሪካ ኅብረት ሥር የፕሪቶሪያ የሰላም ሥምምነት የቁጥጥር፣ ማረጋገጥና ማስከበር ተልዕኮ ቡድን አባል ብርጋዴር ጄኔራል ትሸፖ ማፉዛ በዕደጋ-ሀሙስና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መለስ ዜናዊ ካምፓስ በነበረ ምልከታ ለቀድሞ ታጣቂዎች የሚሰጠው የተሀድሶ ሥልጠና በጥሩ ሂደት እየተከናወነ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
ቅድመ ዝግጅቱ ስኬታማ በሆነው ሂደትም የቀድሞ ታጣቂዎች ሥልጠናቸውን በቀናነት በመከታተል ወደ ቤተሰቦቻቸው መዋሃድ የሚችሉበት ዕድል መፈጠሩን በሚያደርጉት የቁጥጥር፣ ማረጋገጥ፣ ማስከበርና የክትትል ሥራ ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል።
የአፍሪካ ኅብረትም ከጅማሮው አንስቶ ለብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን በሚያደርገው እገዛ ቀጣይነት ያለው የድጋፍ፣ ቁጥጥርና የክትትል ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ጸጥታ ክፍል የፖለቲካ ባለሙያና የቴክኒክ ድጋፍ ቡድን አባል ኢርነስት ናያ ዶሎ በበኩላቸው የዕደጋ-ሀሙስና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ መለስ ዜናዊ ካምፓስ ማዕከላት የቀድሞ ታጣቂዎችን ከመቀበላቸው በፊት የዝግጅት ሥራ ላይ ምልከታ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በማዕከላቱ የምግብ፣ ምዝገባ፣ የባንክ ሂሳብ መክፈቻና አስፈላጊ ማዕከላት ተደራጅተው የቀድሞ ታጣቂዎችን በተገቢው መንገድ እያስተናገዱ እንደሚገኙ ተመልክተናል ብለዋል።
በአፍሪካ ኅብረት የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ሥልጠና የማሳለፍ መርህ መነሻነትም የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚያደርገው ጥረት ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የተሀድሶ ሥልጠና የሚሰጥባቸው የመቀሌና ዕዳጋ-ሀሙስ ማዕከላት በተቀመጠው ዕቅድ መሰረት የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሳካ መንገድ እያስተናገዱ ነው ያሉት ደግሞ በብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን የፕሮግራም ዕቅድና ክትትል ዳይሬክተር ኮሎኔል በላይ አበበ ናቸው።
የተሀድሶ ሥልጠና ተጠቃሚ የቀድሞ ታጣቂዎች በሚኖራቸው የስድስት ቀናት የቆይታ ሂደትም በጥሩ ሁኔታ እየተከታተሉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
በዚህም ዕዳጋ ሀሙስ ማዕከል ለ3ኛ ዙር፥ የመቀሌ ማዕከል ደግሞ ለ5ኛ ዙር እንዲሁም በአዲግራትና መቀሌ ከተማ ዙሪያ ተንቀሳቃሽ ማዕከላት እየተስተናገዱ መሆኑን ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል በመጀመሪያው ምዕራፍ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም ኅዳር 12/2017 ዓ.ም የፌደራል መንግሥት፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ተባባሪና ለጋሽ አሕጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ተወካዮች በተገኙበት የተጀመረው ሥራ በሁለቱ ማዕከላት ተጠናክሮ ቀጥሏል።