በጂንካ ከተማ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጂንካ ከተማ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር እየተካሄደ ነው
ጂንካ፤ ህዳር 28/2017(ኢዜአ)፦ በአሪ ዞን ጂንካ ከተማ ታዋቂ አትሌቶች የተሳተፉበት የስምንት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር እየተካሄደ ነው።
ታህሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም የሚከበረውን የአሪ ህዝብ የዘመን መለወጫ ''የድሽታ ግና'' በዓልን እና የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ እየተካሄደ ባለው የስምንት ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር ላይ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች፣ ከተለያየ አካባቢ የመጡ ሰዎች እና አትሌቶች ተሳትፈዋል።
የአሪ ዞን አስተዳደር ከፋን ኢትዮጵያ ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጀው የሩጫ ውድድር "ታላቁ ሩጫ ለድሽታ ግና ለሰላም እና አንድነት እሮጣለሁ!" በሚል መሪ ሀሳብ በጂንካ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሩ ዓላማ በዋናነት የድሽታ ግና በዓል እሴት የሆኑትን መረዳዳት፣ መተጋገዝ፣ በፍቅር አብሮ የመኖር ባህልን አጉልቶ ማውጣት መሆኑን የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ ገልፀዋል።
ውድድሩ አብሮነትንና ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ ባለፈ በአሪ ዞን እና አጎራባች ዞኖች እድሉን ሳያገኙ ተደብቀው የቀሩ ድንቅ ችሎታ ያላቸውን ተተኪ አትሌቶች እድል ለመስጠት ታስቦ መካሄዱን የፋን ኢትዮጵያ መስራች አትሌት ፋንቱ ሚጌሶ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ አትሌት ፋንቱ ሚጌሶን ጨምሮ ሌሎች አትሌቶች እና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች እና አርቲስቶች ታድመዋል።