የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ያሳደገና ውጤት የተመዘገበበት ነው - አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ያሳደገና ውጤት የተመዘገበበት ነው - አቶ መላኩ አለበል
ባህር ዳር፤ ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፦ ''ኢትዮጵያ ታምርት'' የአገሪቱ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ያሳደገና ውጤት የተመዘገበበት ንቅናቄ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለፁ።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ውጤታማነት አስመልክቶ ከክልሉ ስትሪንግ ኮሚቴ ጋር የውይይት መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።
ሚኒስትሩ አቶ መላኩ እንደገለጹት፤ አሁን የሚስተዋሉ አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት በኢንዱስትሪው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግርን ማረጋገጥ ይገባል።
ማኑፋክቸሪንግ ለአጠቃላይ አገራዊ እድገት፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ ተኪ ምርትን በስፋት ለማምረት፣ ለሥራ እድል ፈጠራና የህዝብን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሰረት እንደሆነም አስገንዝበዋል።
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እመርታዊ ለውጥን በማረጋገጥ የተረጋጋ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና አገራዊ ደህንነትን ማስፈን እንደሚቻል በማመን በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተሰራው ሥራ በአገራችን የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከ47 በመቶ ወደ 60 በመቶ ማሳደግ ተችሏል።
በተጨማሪም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ተዘግተው የነበሩ ከ470 በላይ ኢንዱስትሪዎችን ችግር በመፍታት ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ተደርጓል።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁኔን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ያለውን አቅም ለመጠቀም የሚያስችል ነው።
ንቅናቄው የተቋማትና የአመራሩን ቅንጅታዊ አሰራር በማዳበር በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመንስኤው በመፈተሽ መፍትሄ ማበጀት ያስቻለና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልፀዋል።
በከፍተኛ አመራር እየተመራ ያለው የስትሪንግ ኮሚቴ ንቅናቄው ያመጣውን ትሩፋት ለክልሉ ሁለንተናዊ እድገት መጠቀም የሚያስችል ስራ አጠናክሮ ማስቀጠሉን አስረድተዋል።
በአማራ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንዳሉት፤ ንቅናቄው በአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚታየውን የመሰረተ ልማት፣ የግብዓት፣ የሰው ሃይል አቅርቦትና ሌሎች ችግሮችን በመፍታት የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።
በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ በተደረገ ጥረት 568 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ማምረት ከማሸጋገር ባለፈ በተለያዩ ችግሮች ተዘግተው የቆዩ ከ271 በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።