ቀጥታ፡

የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተሳትፎ እያደገ ነው - አለሙ ስሜ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፦ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

አራተኛው የሲቪክ ማህበራት ሳምንት "ለዘላቂ ሰላም እና ፍትሐዊ ልማት ቃል ኪዳናችንን እናድስ" በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው እለት ተከፍቷል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ለውጡን ተከትሎ ዘርፉን የሚያጠናክሩ የህግ ማሻሻያዎችና የተቋም ሪፎርሞች መደረጋቸውን አንስተው በዚህም የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የልማት እና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተሳትፎ እያደገ ነው ብለዋል።

ድርጅቶቹ የተቋቋሙለትን አላማ ለማሳካት በሚያደርጉት ጥረት መንግስት የተጠናከረ ድጋፍና እገዛ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ተረፈ ደጌቲ፤ አራተኛው የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ከህዳር 27 እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።

የሁነቱ ዋና አላማም የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች እያከናወኗቸው ያሉ ተግባራትን ለማስገንዘብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ሁነቱ በፓናል ውይይቶች፣ ኢግዚቢሽኖች እና ባዛሮች የሚቀርቡበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተደረጉ ማሻሻያዎች የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ያስቻላቸው መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ለተጠናከረ ስራ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም