ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ተተኪ አመራሮችን ማፍራት ትኩረት ተሰጥቶታል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ተተኪ አመራሮችን ማፍራት ትኩረት ተሰጥቶታል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ተተኪ አመራሮችን ማፍራት ላይ ትኩረት መደረጉን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሚኒስትሮች ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአለም ላይ ቀደምት የሀገረ-መንግስት ግንባታ ታሪክ ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
በእነዚህ ዘመናት በርካታ ስልጣኔዎችን ለአለም ያበረከተች ሲሆን ኪነ ህንጻዎች፣ የህክምና ጥበቦችና መሰል ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
ስራዎቹ ለአሁኑ ትውልድ ኩራት ከመሆን አልፈው በቱሪስት መዳረሻነት ከፍተኛ ገቢ እያስገኙ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ በእነዚህ ዘመናት በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበች ቢሆንም ውጣ ውረዶችንም አሳልፋለች፡፡
አሁን ላይ ግን እነዚህን የከፍታና የዝቅታ ጉዞዎች አልፋ በአስተማማኝ የብልጽግና ጎዳና ላይ ትገኛለች።
ከአፍሪካ በጠንካራ ኢኮኖሚ ግንባር ቀደም ሀገር ለመሆን በርካታ ኢኒሼቲቮችንና ፕሮጀክቶችን እያከናወነች ነው።
የተጀመሩ የልማት እና የብልጽግና ጉዞዎችን ለማሳለጥ የአመራር የቅብብሎሽ ሚና የጎላ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ሚኒስትሮች ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደገለጹት በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ተተኪ አመራሮችን ማፍራትና ዘመን የሚሻገሩ ተቋማትን መገንባት ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል።
በሀገራት መካከል ያለው የዕድገት ልዩነት በተፈጥሮ ሃብት፣ በታሪክ፣ በህዝብ ብዛትና በባህል ሳይሆን ተተኪ አመራሮችን በመፍጠርና ተቋማትን ለመገንባት በሰጡት ትኩረት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢኮኖሚያዊ እድገት በአንድ ጀንበር የሚመጣ ሳይሆን በትውልድ ቅብብሎሽ የሚረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ያላትን ፀጋ ተጠቅማ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ሆና እንድትቀጥል ተተኪ አመራሮችን በመፍጠር ረገድ በትኩረት በመሰራት ላይ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሐብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው፤ በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ስኬትን ለማስመዝገብ የሁሉንም ዜጎች ርብርብ የሚጠይቅ ቢሆንም መሪዎች ግን የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዛሬ ለደረሰበት ስኬት የበቃው በመሪዎች ቅብብሎሽ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም የነገ ተተኪ አመራሮችን በየደረጃው ማሰልጠን፣ ማብቃትና እርስ በእርስ ልምድ እንዲለዋወጡ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ተተኪ አመራሮችን ለማፍራት ወጣቶችን በማህበራዊ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ተሳታፊ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ናቸው፡፡
ወጣቶች ወደ መሪነት ከመምጣታቸው በፊት ስለመሪነት ብያኔ እንዲያውቁና መልካም ስብዕና እንዲላበሱ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ሚኒስቴሩ ወጣቶች በአለም አቀፍ መድረኮች እንዲሳተፉና ልምዶችን እንዲወስዱ የማድረግ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በትናንትናው እለት በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ተተኪ እና ነባር አመራሮች የልምድ ልውውጥ መድረክ መካሔዱ ይታወሳል፡፡