ቀጥታ፡

መንግስት ያመቻቸው የኢንቨስትመንት ማበረታቻ የተሻለ እንድንሰራ አድርጎናል - የጎንደር ከተማ ባለሃብቶች

ጎንደር፤ ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ መንግስት ባመቻቸላቸው የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ስርዓት ታግዘው በተሰማሩበት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ወደ ማምረት እየተሸጋገሩ መሆናቸውን የከተማው ባለሀብቶች ተናገሩ።

''ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት'' በሚል መሪ ሀሳብ ባለሃብቶችን ያሳተፈ መድረክ ተካሂዷል።

በከተማው በኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ ይርጋ ነጋሽ እንዳሉት በ70 ሚሊዮን ብር ካፒታል የጋቢዮን ሽቦና የባለቆብ ምስማር ማምረቻ ፋብሪካ ገንብተው በመንቀሳቀሰ ላይ ይገኛሉ።

በመንግስት በኩል በተደረገላቸው ሁለንተናዊ እገዛ በአሁኑ ወቅት የህንጻ ግንባታና የማሽን ተከላ ስራው በማጠናቀቅ የሙከራ ምርት ለመጀመር በሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፋብሪካው በቅርቡ ወደ ማምረት ሲሸጋገርም ለ35 ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ ከልማት ባንክ በሊዝ ፋይናንስ የማምረቻ ማሽን ድጋፍ እንደተደረገላቸውም ተናግረዋል።

ሌላው ባለሃብት አቶ አያናው የኔሰው በበኩላቸው፤ በ27 ሚሊዮን ብር ካፒታል በከተማው በሚገኘው የኢንዱስትሪ መንደር ከልማት ባንክ በሊዝ ፋይናንስ በብድር ባገኙት የማምረቻ ማሽን የቤት ክዳን ቆርቆሮ የሙከራ ምርት ማምረት ጀምረዋል።

ፋብሪካቸው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ለ75 ሰዎች የስራ እድል አንደሚፈጥርና በዚህም ከውጪ የሚገባውን የቤት ክዳን ቆርቆሮና ምስማር በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት የውጪ ምንዛሬ ለማዳን መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

በከተማው የሰፈነው አስተማማኝ ሰላም ለአምራች ኢንዱስሪው ዘርፍ መነቃቃት መፍጠሩን ጠቁመው፤ የፋይናንስ ተቋማት ለባለሀብቶች እያደረጉ ያለውን የብድር አቅርቦት ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡


 

በጎንደር ከተማ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶችን ወደ ምርት ስራ ለማስገባት የተለያየ ድጋፍ እየተደረገ ነው ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ግርማይ ልጃለም ናቸው።

ድጋፉ የሚሰጠውም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመሰማራት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለወሰዱና በቅድመ ግንባታ እንዲሁም በግንባታ ሂደት ላይ ለሚገኙ 213 ፕሮጀክቶች እንደሆነ ገልፀዋል።

ፕሮጀክቶቹ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በተሟላ መንገድ ወደ ማምረት ሲገቡም ለ17 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል የመፍጠር አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል።

ባለሃብቶቹን በመደገፍም ባለፉት አምስት ወራት ለ13 ፕሮጀክቶች ስምንት ሄክታር የግንባታ ቦታ መሰጠቱን ጠቁመው፤ ለ12 ባለሀብቶች ደግሞ ከ761 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መመቻቸቱን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ወደ ማምረት የተሸጋገሩ ኢንዱስትሪዎች ከሁለት ሺህ ቶን በላይ የግብርና ምርቶች ወደ ውጪ በመላክ ከዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሬ ማስገኘታቸውን ጠቅሰው፤ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በመተካትም ከሰባት ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሬ ማዳን እንደተቻለም ገልፀዋል።

ባለሃብቶቹ በስራ እንቅስቃሴ ያጋጠሟቸውን መሰረታዊ ችግሮች በቅንጅት በመፍታት በፍጥነት ወደ ምርት ስራ የሚገቡበት አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጠርም አረጋግጠዋል።

በምክክር መድረኩ የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት፣ የከተማው ውሃ አገልግሎት ጽህፈት ቤትና ሌሎች አጋር አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም