ሙሽራዋ አርባ ምንጭ እንግዶቿን እያስተናገደች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሙሽራዋ አርባ ምንጭ እንግዶቿን እያስተናገደች ነው
ሙሽራዋ አርባ ምንጭ እንግዶቿን እያስተናገደች ነው
የሰላም፣ የመቻቻል፣ የፍቅርና የአብሮነት ተምሳሌት ውቢቷ አርባ ምንጭ 19ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በድምቀት እንዲከበር ዝግጅቷን አጠናቃ እንግዶቿን እየተቀበለች ነው።
በእርጥብ ሳር ፀብን የሚያበርዱት የጋሞ አባቶች ምድር፤ አባቶችን የሚሰሙ የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶች ያሉባት ናት - አርባ ምንጭ።
ለሰው ልጆች የሁሉም መሠረት ሰላም ነው፤ ከሰላም የሚልቅ ፀጋ የለምና ጋሞዎች ሰላምን ማጣጣምን አበክረው ይወዳሉ።
አርባ ምንጭ ከተማ በአዲሷ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ካሉ ስድስት ማዕከል ከተሞች አንዷ ናት። አርባ ምንጭ የጋሞ፣ የዘይሴና የጊዲቾ ነባር ብሔረሰቦች መዲና ናት። ልዩ ልዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ተደጋግፈው፣ ተፋቅረውና ተጋብተው የሚኖሩባት የትንሿ ኢትዮጵያ ተምሳሌት ተደርጋም ትታያለች።
"ከአርባ ምንጭ ውሃ ብቻ ሳይሆን ሰላምና ፍቅርም ይፈልቃል" የሚባለውም ለዚህ ነው።
አንድም የሙዝ፣ የአቦካዶ፣ የማንጎ ሀብቶቿ የፍራፍሬ ቅርጫት አስብለዋታል፤ አንድም ደግሞ መስህቦቿ የቱሪስት መናገሻ ምድረ ገነት አድርጓታል።
የስሟ ስያሜ መነሻ የሆኑት ከአርባ በላይ ምንጮች ባለቤት አርባ ምንጭ የጋንታ ተራራን ተንተርሳ የአባያና ጫሞ ሀይቆችን በግራዋ አድርጋ፣ የዓዞ ራንች ይዛ፣ በነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርኮች ደምቃ የአገር ውስጥና የባህር ማዶ ቱሪስቶችን በማስተናገድ ተጠምዳለች።
ወትሮም ምድረ ገነቷ አርባ ምንጭ ይበልጥ ተውባና ደምቃ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ታዳሚ እንግዶቿን መቀበል ጀምራለች። በአሁኑ ወቅት አርባ ምንጭ "ቀኑም ቀን ነው፤ ምሽቱም ቀን ነው" ጨለማው ለእንግዶቹ ስፍራን ለቆ የሸሸ ይመስላል።
ወጣቶች፣ ሴቶችና የአገር ሽማግሌዎች በኢትዮጵያዊ ባህል እንግዶቻቸውን ለመቀበል በየፊናቸው ተሰማርተዋል።
ጫማ ከሚያስውበው ጎበዝ እስከ አቅጣጫ ጠቋሚው ድረስ "ቤታችን ቤታችሁ" በሚል የተለያዩ እንግዶችን ተቀብሎ ለማሳደር ዝግጁ ሆኗል።
እንግዶቿ ሰላሟን እንዲያጣጥሙ፣ በፍቅሯ ሀሴት እንዲያደርጉና በቱርስት መስህቦቿ እንዲደመሙ ለማድረግ አርባ ምንጭ ዝግጅቷን አጠናቃለች።
ለእንግዶች ማረፊያ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ ሎጆችና ሪዞርቶች በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተዋል።
አርባ ምንጮችን፣ የአባያና ጫሞ ሀይቆችን፣ የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክን፣ የዓዞ ራንችን፣ ባህላዊና ድንቅ የሆነው የዶርዜ መንደርን እንድሁም የጋሞዎች የሸማ ጥበብ፣ የአርባ ምንጭ ደንና ሌሎች ለጎብኚዎች ክፍት ሆነዋል።
በዚህ ልዩ ዕድል ለመጠቀም በማሰብ አስቀድመው ወደ ከተማዋ የገቡ እንግዶች የቱርስት ፀጋዎቿን በማየት መልካም ጊዜ ማሳለፍ ጀምረዋል።
ጋሞዎች የሰላም፣ የአብሮነትና የፍቅር መሠረትና ፀብን በእርጥብ ሣር የሚያበርዱበት የእርቅ ምልክት የሆነውን የ"ዱቡሻ" ስርዓት ለእንግዶች ለማካፈል ዝግጁ ናቸው።
"አገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የተለያዩ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችን የሚያገናኝ መድረክ በመሆኑ የህዝቡን አብሮነትና አንድነት ይበልጥ ያጠናክራል።
"እኛ ኢትዮጵያዊያን በጋብቻ ፣ በሃይማኖት ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አንዳችን ያለ አንዳችን መኖር እስከማንችል የተጋመድንና የተሳሰርን ህዝቦች ነን" የሚለውን ሀሳብ በአንድነትና በአብሮነት ለማጽናት አጋጣሚው መልካም ነው። እውነትነቱንም የሚያንጸባርቅ የአንድነትና የአብሮነት መገለጫ ነው።
በዚህ ዘመን የውስጥ አንድነታችን ከጠነከረ የውጭ ጠላት አይደፍረንም። በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ተሰሚነታችን እየጨመረ የአገራችን ገጽታ እየፈካ ይሄዳል።
የኢትዮጵያ 19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የሚገናኙበት ታሪካዊ መድረክ በመሆኑ ፍቅራችን ፣ አንድነታችን ፣ አብሮነታችን ፣ ወዳጅነታችን ፣ ወንድማማችነታችንና እህትማማችነታችን ይበልጥ የሚጠናከርበት ዕለት ነው።