የመዲናዋ ዓለም አቀፍ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል እየሆነች መምጣት የአገልግሎት ዘርፉን እያነቃቃ ነው - የሆቴልና የፋይናንስ ተቋማት - ኢዜአ አማርኛ
የመዲናዋ ዓለም አቀፍ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል እየሆነች መምጣት የአገልግሎት ዘርፉን እያነቃቃ ነው - የሆቴልና የፋይናንስ ተቋማት
አዲስ አበባ፤ ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል እየሆነች መምጣቷ የአገልግሎት ዘርፉን እያነቃቃ እንደሚገኝ የሆቴልና የፋይናንስ ተቋማት ገለጹ።
በከተማዋ የተገነቡ አዳዲስ የመስህብ ስፍራዎችና የኮሪደር ልማትም የጎብኚዎችንና የኮንፍረንስ ተሳታፊዎችን ቆይታ ለማራዘም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።
በአዲስ አበባ መደበኛ አህጉራዊ ስብሰባ መካሄድ የጀመረው እ.ኤ.አ በ1963 አፍሪካውያን በጋራ ነጻነታቸው ጉዳይ በመከሩበትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመሰረቱበት ወቅት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
መዲናዋ የአፍሪካ ህብረትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ ላለፉት አስርት ዓመታት ታላላቅ ስብሰባዎችን እያስተናገደች ትገኛለች።
በመዲናዋ የሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች በየጊዜው እየጨመሩ ሲሆን ለሆቴሎች፣ ለባህላዊ አልባሳትና ስጦታ መሸጫ ሱቆች እንዲሁም ባንክን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሰፊ የገበያ ዕድልን እያመጡ ይገኛሉ።
የስብሰባው ተሳታፊዎች በሚቆዩባቸው ቀናት ለሆቴል፣ ለምግብና ለልዩ ልዩ ወጪዎች የሚያውሉት የውጭ ምንዛሬ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ዕድገት ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የከተማዋን የአፍሪካ መዲናነትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫነት የምትመጥንና የኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አሸናፊ ሙሉጌታ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ዘርፉ ልማት እየሰጠች ያለው ትኩረት ተጨባጭ ውጤት እየታየበት ነው።
አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን በማስፋትና ለነባሮቹ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ረገድም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ዘርፉን ከማነቃቃት አኳያ ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።
የሲድራ ኢንተርናሽናል ሆቴል ጀነራል ማናጀር ዳኙ ጌቱ እንደሚሉት፣ መዲናዋን ጨምሮ ከተሞችን ለማስዋብ የተጀመሩ ተግባራት ለዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮምፕሊያንስ ዳይሬክተር ጋዲሳ ተሾመና የዳሽን ባንክ ኮምፕሊያንስ ስራ አስኪያጅ ግርማ ይዳኘ የአዲስ አበባን ለውጥ ተከትሎ እየተካሄዱ ያሉ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ለአገልግሎት ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩን ተናግረዋል።
መዲናዋ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል እየሆነች መምጣቷ ከሀገር ገጽታ ግንባታ ባለፈ ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አሸናፊ ሙሉጌታ እና የሲድራ ኢንተርናሽናል ሆቴል ጀነራል ማናጀር ዳኙ ጌቱ፥ በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን ዓለም አቀፍ ስብሰባ የሚመጥን አገልግሎት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የእንግዶችን ፍላጎት ያማከለ አገልግሎት ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ እስከ መዳረሻ መስጠት እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።
ይህን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀምና የእንግዶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምቹ የቢዝነስ ስትራቴጂ ነድፈው መተግበር አለባቸው ብለዋል።
ከኮንፍረንሱ ጎን ለጎን እንግዶች የኢትዮጵያን ባህልና ከተማዋን በአግባቡ እንዲያውቁ ማድረግ ላይ በጋራ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።