በአማራ ክልል የልጅነት ልምሻ/ፖሊዮ/ መከላከያ ክትባት በዘመቻ መስጠት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የልጅነት ልምሻ/ፖሊዮ/ መከላከያ ክትባት በዘመቻ መስጠት ተጀመረ
ባህር ዳር፤ ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ከ4 ሚሊዮን የሚበልጡ ሕፃናትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለተኛው ዙር የልጅነት ልምሻ/ፖሊዮ/ መከላከያ ክትባት በዘመቻ መስጠት መጀመሩን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ክትባቱ የተጀመረው በባህር ዳር ከተማ በፋሲሎ አፀደ ሕፃናት የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ነው።
በዚህ ወቅት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ እንደገለጹት፤ የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት ያላገኙ ሕፃናትን ለዘላቂ የአካል ጉዳት ከማድረስ ባለፈ ለህልፈተ ሞት የሚዳርግ በሽታ ነው።
ለዚህም በክልሉ ከህዳር 27 እስከ 30/2017 ዓ.ም በሚቆየው የክትባት ዘመቻ ከ4 ሚሊዮን የሚበልጡ ሕፃናትን ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ ክትባት መስጠት መጀመሩን አስታውቀዋል።
በክትባት ዘመቻው ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሁሉም ሕፃናት ከዚህ ቀደም ቢከተቡም ባይከተቡም ክትባቱ እንዲወስዱ መደርግ እንዳለበት አሳስበዋል።
ክትባቱ በትምህርት ቤት፣ ቤት ለቤት፣ በህፃናት ማቆያና በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ ለክትባቱ ስኬታማነት የሃይማኖት አባቶች፤ መምህራን፣ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው እንዳመለከቱት፤ የልጅነት ልምሻ /ፖሊዮ/ ለመከላከል ለረጅም ዓመታት ክትባቱ በመሰጠቱ በሽታው እየቀነሰ መጥቷል።
በሽታውን ሙሉ በሙሉ ከሀገራችን ለማጥፋትም ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሁሉም ሕፃናት ክትባቱን እንዲያገኙ ሁለተኛው ዙር የልጅነት ልምሻ ክትባት ዘመቻ መጀመሩን ተናግረዋል።
ሕፃናት ከበሽታው እንዲጠበቁ በሚሰጠው በዚሁ ክትባትም የጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት ሲመጡ ሁሉም ወላጆች አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ልጆቹን እንዲያስከትብም አሳስበዋል።
ሕፃናት ክትባቱ በአግባቡ እንዲያገኙ ቤት ለቤት በመዞር ህብረተሰቡን በማስተማር ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የጤና ባለሙያ የሆኑት አዲስ ውብሊቀር ናቸው።
በክትባት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የፌዴራል፣ የክልልና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አመራ አባላት፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።