የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር መካከል የተደረሰው የሠላም ስምምነት ለዘላቂ ሰላም ጥሩ መሰረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር መካከል የተደረሰው የሠላም ስምምነት ለዘላቂ ሰላም ጥሩ መሰረት ነው

አዲስ አበባ፤ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፦የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ከፍተኛ አመራር መካከል የተደረሰው የሠላም ስምምነት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ጥሩ መሰረት መሆኑን የኦሮሚያ የሃይማት ተቋማት ጉባዔ ገለጸ።
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አመራር የነበሩት ጃል ሰኚ ነጋሳ መንግስት ያቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሸገር ከተማና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ እና የኦሮሚያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቦርድ ሰብሳቢ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ፤ የኦሮሚያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና የኦሮሚያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ኡስታዝ ጋሊ ሙክታር መግለጫውን ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የተደረገው የሠላም ስምምነት በግጭት ሳቢያ ተራርቀው የቆዩትን ያቀራረበ እና ለዘላቂ ሰላም ጥሩ መሰረት ያኖረ በመሆኑ ምስጋና ቀርቧል።
የሰላም ስምምነቱ በተለይም ለኦሮሞ ህዝብ ሰላም ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን አንስተው፥ ለዘላቂነቱ ሁሉም በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ጉባኤው አመላክቷል።
የተደረሰው የሠላም ሥምምነት ከጠመንጃ ይልቅ የሰለጠነ አማራጭን የተከተለ የሚደነቅና የሚበረታታ በመሆኑ ሁሉም ሊደግፈው ይገባል ነው ብሏል።
ጉባኤው እርቅና ሰላም እንዲሰፍን ተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡን በማስታወስ በቀጣይም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።
የሰላም ጥሪዎችን በመቀበል ወደ ሰላም ስምምነት በመምጣታቸው እናደንቃለን፣ እናመሰግናለንም ብለዋል።
የሰላም ጉዳይ የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በትብብር እንስራ በማለትም የኦሮሚያ የሃይማት ተቋማት ጉባዔ ጥሪ አቅርቧል።