ቀጥታ፡

በህዝባዊ ውይይቶችና በጥናት የተለዩ የሙስናና ብልሹ አሰራር ችግሮችን በዘላቂነት ለማስወገድ እንደሚሰራ ተገለጸ

ቡታጅራ፤ ህዳር 27/2017 (ኢዜአ):- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በህዝባዊ ውይይቶችና በጥናት የተለዩ የሙስናና ብልሹ አሰራር ችግሮችን በዘላቂነት ለማስወገድ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ትግል እንደሚደረግ የክልሉ የጸረ ሙስና ግብረ ሃይል አስታወቀ።

የግብረ ሃይሉ ሰብሳቢና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ሌብነትና ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ ቅንጅታዊ ጥረት ያስፈልጋል።

የክልሉ መንግስት ሙስናና ብልሹ አሰራር በሃገር ሃብትና በለውጥ ጉዞ ላይ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመከላከል ሰባት አባላት ያሉት ግብረ ኃይል አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

ግብረ ኃይሉ በህዝባዊ ውይይትና በጥናት የተለዩ የሙስናና ብልሹ አሰራር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ህብረተሰቡን ያሳተፈ ትግል እንደሚያጠናከር ተናግረዋል።

በክልሉ በከተማና በገጠር በመሬት ላይ የሚፈጸም ሌብነትና ብልሹ አሰራሮች መኖራቸውን መለየቱን ጠቅሰው በገጠር በወል መሬቶችና በደን ይዞታዎች፣ በህብረት ስራ ማህበራትና በተቋማት ይዞታዎች ላይ ችግሩ ጎልቶ እንደሚታይ ገልጸዋል።

በከተሞች የስራ እድል ለተፈጠረላቸው ኢንተርፕራዞች የተዘጋጁ የመስሪያና መሸጫ ቦታዎችን ለሶስተኛ ወገን በማስተላለፍ የመንግስትና የህዝብ ሃብት እንደሚመዘበርም ተናግረዋል።

በሃሰተኛ ሰነድ በባለይዞታና በልማት ተነሽዎች ስም የሚከናወን የመሬት ወረራና ሌሎች ብልሹ አሰራሮች መኖራቸውን ግብረሃይሉ በማረጋገጡ የትግሉ የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል ብለዋል።

ከገቢ ንግድ ጋር የተያያዙ ብልሹ አሰራሮችና ሌብነቶችም የግብረ ሃይሉ ተጨማሪ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ጠቅሰው በሀሰተኛ ሰነዶች ገቢ ለመሰወር የሚደረጉ ህገወጥ ተግባራት መኖራቸውንም ገልጸዋል።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች በባለሙያው፣ በአመራሩና በባለሃብቱ ቅንጅት የሚፈጸሙ በመሆናቸው ግብረ ኃይሉ ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት የሚታገላቸው የትኩረት ዘርፎች ናቸው ብለዋል።

ግብረ ሃይሉ ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች በተጨማሪ ከህዝቡ ከቀረቡ ጥቆማዎች መካከልም በመንግስትና በህዝብ ሃብት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚደረግም ጠቅሰዋል።

አዳዲስ ጥቆማዎችን በመቀበልና ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ በሚደረግ ጥናት መሰረትም እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ ከታህሳስ 1/ 2017 ዓም ጀምሮ ግብረ ኃይሉ በሚያዘጋጃቸው ነጻ የስልክ መስመሮች፣ በአካል፣ በጽሁፍና በሰነድ ጥቆማ በማቅረብ በትብብር እንዲሰራም ጠይቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም