19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓልን ለመታደም ወደ ስፍራው ላቀኑ ታዳሚዎች በወላይታ ሶዶ አቀባበል ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓልን ለመታደም ወደ ስፍራው ላቀኑ ታዳሚዎች በወላይታ ሶዶ አቀባበል ተደረገ
ሶዶ፤ ህዳር 27/2017(ኢዜአ)፡- 19ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓልን ለመታደም ወደ ስፍራው ላቀኑ ከመላ ሀገሪቱ ለተውጣጡ የበዓሉ ተሳታፊዎችና የክልል የባህል ቡድኖች በወላይታ ሶዶ ከተማ አቀባበል ተደረገላቸው።
ትላንት ማምሻውን ለበዓሉ ተሳታፊዎች አቀባበል ያደረጉላቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የወላይታ ዞንና የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር አመራር አባላትና የከተማዋ ነዋሪዎች ናቸው።
በዓሉ የተለያየ ስያሜ በተሰጣቸው ቀናት እየተከበረ የሚገኝ ሲሆን፤ "የደቡብ ኢትዮጵያ ቀን"ን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የባህል ፌስቲቫልም በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።
ለበዓሉ ተሳታፊዎች በተዘጋጀው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወላይቴ ቢተው እንግዶቹን "እንኳን ደህና መጣችሁ" ብለዋል።
የዘንድሮውን በዓል በተሳካ መልኩ ለማሰናዳት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ እንግዶቹን በደስታ መቀበል መጀመሩን ጠቁመዋል።
በመሆኑም የበዓሉ ተሳታፊዎች በቆይታቸው ያላቸውን ቱባ ባህልና ማንነት በአግባቡ በማንጸባረቅ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት በጽናት እንዲቆሙ አስገንዝበዋል።
"የበዓሉ ክብር መገለጫ እናንተ ናችሁ" ያሉት ምክትል አፈ ጉባዔዋ፤ "በቆይታችሁ ተደስታችሁና ዓላማችሁን አሳክታችሁ እስክትመለሱ ድረስ የክልሉ መንግሥት ከጎናችሁ አይለይም" ብለዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጴጥሮስ ወልደማሪያም በበኩላቸው፤ ወደ ወላይታ ሶዶ ከተማ የገባችሁ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ተወካዮች በመሆናችሁ ልዩ ክብር ይገባችኋል ብለዋል።
በዓሉን ለማክበር በአንድ መድረክ ላይ በመገናኘታችን ደስታ ይሰማናል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ በተለይ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተገኙ ስኬቶችን ማስቀጠል ከሁሉም እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ በዓሉ የአብሮነት አቅም በመሆኑ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለማጎልበት፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታችንን አጠናክረን ለማስቀጠል እንጠቀምበታለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
ወላይታ ሶዶ ከተማ በሚያስገቡ ሰባቱም በሮች በዓሉን ለማክበር የሚገቡ እንግዶችን በጨዋ የኢትዮጵያ ባህሎች እየተቀበሉ መሆናቸውን የተናገሩት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ፍሬው ሞገስ (ዶ/ር) ናቸው።
የከተማዋ ነዋሪዎች በከፍተኛ ዝግጅት የበዓሉ ታዳሚዎችን እየተቀበሉና እያስተናገዱ እንዲሁም ባህሉንም እየተለዋወጡ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ በዚህም ደስታና ኩራት ይሰማናል ብለዋል።
ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የተውጣጡ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህል ቡድን አባላት የየራሳቸውን ባህል፣ ዕሴት እና ማንነት በሚገልጽ ባህላዊ አልባሳት ተጊጠው፣ በባህላዊ ጭፈራዎች ደምቀው አምሽተዋል።