በክልሉ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
ባህር ዳር፤ ህዳር 27/2017 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የአካባቢ ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ።
"የአርብ ጠንካራ እጆች የወባ ወረርሽኝን ይገታሉ" በሚል መሪ መልዕክት የክልሉ፣ የከተማ አስተዳደሩና የፌዴራል አመራር አባላት የተሳተፉበት የአካባቢ ቁጥጥር ስራ በባህር ዳር ከተማ ጣና ክፍለ ከተማ ተካሂዷል።
በምክትል ርዕሰ መተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የክረምቱን መውጣት ተከትሎ የወባ በሽታ ስርጭት የመስፋፋት ምልክት እያሳየ ነው።
የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሁሉም ህብረተሰብ የአካባቢ ቁጥጥር ስራን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።
የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በበኩላቸው፤ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ከመስከረም አጋማሽ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የአካባቢ ቁጥጥር ስራ በንቅናቄ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተስብ ጤና ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ ፤ የወባ በሽታን ለመከላከል የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን በማፋሰስና በማዳፈን መከላከል ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ህብረተሰቡን በስፋት ማሳተፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለህብረተሰቡም ስለ አጎበር አጠቃቀም ግንዛቤ በመፍጠር በሽታውን ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በከተማው የወባ በሽታን ለመከላከል ህብረተሰቡን በማስተባበር በሳምንት አንድ ቀን በንቅናቄ የአካባቢ ቁጥጥር ስራ በዘመቻ እየተካሄደ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ ናቸው።
ህብረተሰቡም ለወባ መራቢያ አመቺ የሆኑ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን ማፋሰስና በማዳፈን የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቀነስና ለመከላከል የዘወትር ተግባሩ አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአካባቢ ቁጥጥር የንቅናቄ ስራውም የክልል፣ የፌዴራልና የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።